ማስተስረይ (Expiation) እና ቍጣ ማብረድ (Propitiation) ምን ማለት ናቸው?

16 ሐምሌ 2026

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔር በግ

16 ሐምሌ 2026

ማስተስረይ (Expiation) እና ቍጣ ማብረድ (Propitiation) ምን ማለት ናቸው?

16 ሐምሌ 2026

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔር በግ

16 ሐምሌ 2026

በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ጸሎት ያለው ስፍራ

የክርስቲያን ሕይወት ግቡ ምንድን ነው? የክርስቲያን ሕይወት ግቡ፣ለክርስቶስ በመታዘዝ የሚገኝ እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ነው። መታዘዝ፣ የክርስትናን በረከቶች የሚከፍት ቊልፍ ነው። ጸሎት ደግሞ ለመታዘዝ የሚያነሣሣና መታዘዝን የሚያለመልም፣ ልብም ለመታዘዝ እንዲሻ ትክክለኛውን “የአእምሮ ዝግጁነት” እንዲይዝ የሚያደርግ ነው።

ርግጥ ነው፣ ዕውቀትም እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ያለ ዕውቀት እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ማወቅ አንችልም። ይሁን እንጂ፣ በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋራ ኅብረት ካላደረግን በቀር፣ ዕውቀትና እውነት ረቂቅ [Abstract] ሐሳቦች ሆነው ይቀራሉ። የእግዚአብሔርን ቃል የሚያስተምረን፣ የሚያነሣሣንና የሚያበራልን መንፈስ ቅዱስ ነው። እርሱ የእግዚአብሔርን ቃል ለእኛ ያስተላልፋል፤ ለአብም በጸሎት ምላሽ እንድንሰጥ ይረዳናል።

ጸሎት በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ስፍራ አለው። በመጀመሪያ፣ ለደኅንነት እጅግ አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ሰዎች መስማት አይችሉም፤ ደንቆሮ ቢሆኑም እንኳ ሊድኑ ይችላሉ። አንዳንዶች ማየት አይችሉም፤ ዕውር ቢሆኑም እንኳ ሊድኑ ይችላሉ። የመልካሙ ዜና ዕውቀት ይኸውም፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሞትና ትንሣኤ የሚገኘው ደኅንነት ከአንዱ ወይም ከሌላው ምንጭ ሊመጣ ይችላል፤ በስተመጨረሻ ግን፣ አንድ ሰው በትሕትና ከእግዚአብሔር ደኅንነትን መለመን አለበት። የደኅንነት ጸሎት እግዚአብሔር እሰማዋለሁ ያለው ብቸኛው የኀጢአተኛው ጸሎት ነው።

በሰማይ ያሉ ቅዱሳን የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? በርካታ ነገሮች አሉ። ሁሉም በክርስቶስ የስርየት ሞት በማመናቸው ጽድቀዋል። ሁሉም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነው። እንዲሁም ሁሉም ለደኅንነት ጸልየዋል። ያለ ጸሎት መሆን ማለት ያለ እግዚአብሔር፣ ያለ ክርስቶስ፣ ያለ መንፈስ ቅዱስ፣ እንዲሁም ያለ ሰማይ ተስፋና እውነታ መኖር ማለት ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ የአንድ ክርስቲያን ዋነኛው መታወቂያ የጸሎት ሕይወቱ ነው። አንድ ሰው እየጸለየ ክርስቲያን ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሳይጸልይ ክርስቲያን ሊሆን ከቶ አይችልም። ሮሜ 8፥15 የእግዚአብሔር ልጆች ያደረገን ያ መንፈሳዊ የማደጎ ልጅነት፣ “አባ! አባት” ብለን በቃል እንድንጮኽ እንደሚያደርገን ይነግረናል። ጸሎት ለክርስቲያን ሕይወት ልክ እንደ እስትንፋስ ነው፤ ሆኖም እንደ ጸሎት ያለ ችላ የተባለ ክርስቲያናዊ ተግባር የለም።

ጸሎትን፣ ቢያንስ የግል ጸሎትን፣ በተሳሳተ ውስጣዊ ተነሣሥቶት ማድረግ ከባድ ነው። አንድ ሰው እንደ ሐሰተኛ ነቢያት በተሳሳተ ውስጣዊ ፍላጎት ተነሣሥቶ ሊሰብክ ይችላል። እንዲሁም በተለያዩ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በተሳሳተ ተነሣሥቶት ሊሳተፍ ይችላል። ብዙዎቹ የሃይማኖት ውጫዊ ገጽታዎች በተሳሳተ ተነሣሥቶት ሊከናወኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን አንድ ሰው በተሳሳተ ተነሣሥቶት ከእግዚአብሔር ጋራ ኅብረት ያደርጋል ብሎ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው። ማቴዎስ 7 በዚያች “የመጨረሻ ቀን” ብዙዎች በፍርድ ፊት ቆመው በስሙ ስላደረጓቸው ታላላቅና ክቡር ተግባራት ለክርስቶስ እንደሚነግሩት ይነግረናል፤ የርሱ ምላሽ ግን “ከቶ አላውቃችሁም” የሚል ይሆናል።

ስለዚህ እንድንጸልይ ተጋብዘናል፣ እንዲያውም ታዘዝናል። ጸሎት ዕድልም፣ ግዴታም ነው። ማንኛውም ግዴታ ደግሞ አድካሚ ሊሆን ይችላል። ጸሎት እንደ የትኛውም የክርስቲያን ዕድገት መሣሪያ ሥራን ይጠይቃል። በአንድ በኩል፣ ጸሎት ለእኛ ለወደቅን ፍጥረታት ተፈጥሯዊ አይደለም። ምንም እንኳ የተፈጠርነው ከእግዚአብሔር ጋራ ኅብረትና ትውውቅ እንድናደርግ ቢሆንም፣ የውድቀት ውጤቶች ግን አብዛኞቻችንን እንደ ጸሎት ባለ እጅግ አስፈላጊ ነገር ላይ ሰነፎችና ግዴለሾች አድርጎናል። ዳግም ልደት ከእግዚአብሔር ጋራ ኅብረት ለማድረግ አዲስ ፍላጎትን ይጭራል፤ ኀጢአት ግን መንፈስን ይቃወማል።

እግዚአብሔር ልባችንን እንደሚያውቅና ከከንፈራችን ከሚወጡት ቃላት ይልቅ በውስጣችን ያለውንና ያልተነገረውን ልመናችንን እንደሚሰማ በማወቅ መጽናናት እንችላለን። የነፍሳችንን ጥልቅ ስሜት መግለጽ ባቃተን ጊዜ፣ ወይም ስለ ምን መጸለይ እንዳለብን ግራ በሚገባን ጊዜ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ይማልዳል። ሮሜ 8፥26-27 እንዲህ ይላል፦

“እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና።”

በአንድ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ወይም ስለ ምን መጸለይ እንዳለብን በማናውቅበት ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል። ከዚህ ጥቅስ የምንረዳው፣ እኛ በተሳሳተ መንገድ ብንጸልይ እንኳ፣ መንፈስ ቅዱስ ጸሎታችንን ወደ አብ ከመውሰዱ በፊት ስሕተቱን እንደሚያርመው የምናምንበት ምክንያት አለ፤ ምክንያቱም ቍጥር 27፣ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳል” ይላልና።

ጸሎት የቅድስና ምስጢር ነው፤ በርግጥ ቅድስና ምስጢር ካለው ማለቴ ነው። ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን ሕይወት ብንመረምር፣ ታላላቅ የጸሎት ሰዎች እንደ ነበሩ እንረዳለን። ጆን ዌስሊ በቀን ቢያንስ አራት ሰዓት በጸሎት የማያሳልፉ አገልጋዮችን ትልቅ ግምት አይሰጣቸውም ነበር። ማርቲን ሉተር ደግሞ በጣም ሥራ በሚበዛበት ቀን ለሁለት ሰዓት፣ በሌላው ጊዜ ደግሞ በየቀኑ ለአንድ ሰዓት ዘወትር እንደሚጸልይ ተናግሯል።

ጸሎትን ችላ ማለት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ የመቀንጨር ዋነኛው ምክንያት ነው። በሉቃስ 22፥39-62 ያለውን የጴጥሮስን ምሳሌ ተመልከቱ። ኢየሱስ እንደ ልማዱ ሊጸልይ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደና ደቀ መዛሙርቱን፦ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ግን በምትኩ ተኝተው ተገኙ። ቀጥሎ ጴጥሮስ ያደረገው ነገር የሮማን ጦር በሰይፍ ለመጋፈጥ መሞከር ነበር፤ ከዚያም ክርስቶስን ካደ። ጴጥሮስ አልጸለየም፤ በውጤቱም በፈተና ውስጥ ወደቀ። በጴጥሮስ ላይ የሆነው እውነት በእኛም በሁላችን ላይ ይሠራል፦ በአደባባይ ከመውደቃችን በፊት በግላችን (በጓዳችን) እንወድቃለን።

ትክክለኛ ወይም የተሳሳተ የጸሎት ጊዜ አለ? ኢሳይያስ 50፥4 እግዚአብሔር በየዕለቱ የመጸለይን ፍላጎትና በርሱ ላይ የታደሰ መታመንን ስለሚሰጥበት ስለ ጠዋት ጊዜ ይናገራል። ነገር ግን በቀኑ ክፍሎች ሁሉ ውስጥ ስለሚደረጉ የጸሎት ጊዜያት የሚናገሩ ሌሎች ክፍሎችም አሉ። የቀኑ አንዱ ክፍል ከሌላው ይልቅ የተለየ ቅድስና ያለው ተደርጎ አልተለየም። ኢየሱስ በጠዋት፣ በቀን፣ አንዳንዴም ሌሊቱን ሙሉ ይጸልይ ነበር። እርሱ ለጸሎት የተለየ ጊዜ እንደ ነበረው የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ሆኖም ኢየሱስ ከአብ ጋራ የነበረውን ግንኙነት ስናስብ፣ በመካከላቸው ያለው ኅብረት ከቶ እንደማይቋረጥ እናውቃለን።

አንደኛ ተሰሎንቄ 5፥17፣ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ብሎ ያዝዘናል፤ ይህም ማለት ከአባታችን ጋራ በማያቋርጥ ኅብረት ውስጥ መሆን አለብን ማለት ነው።


ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው

አር. ሲ. ስፕሮል

አር. ሲ. ስፕሮል

ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች ሲሆን በፍሎሪዳ ሳንፎርድ በሚገኘው በሴንት አንድሪው ቻፕል ውስጥ በስብከትና በትምህርት የሚያገለግል የመጀመሪያው አገልጋይ፣ የሪፎርሜሽን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የቴብልቶክ መጽሔት ዋና አርታዒ ነበር። Renewing Your Mind የተሠኘው የራዲዮ ፕሮግራሙ በየዕለቱ በዓለም ላይ በሚገኙ በመቶዎች በሚቈጠሩ የራዲዮ ጣቢያዎችና በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት አሁንም ድረስ ይደመጣል። The Holiness of God, Chosen by God እና Everyone’s a Theologian የሚሉትን ጨምሮ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጸጽ አልቦነት በመከላከልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በቃሉ ላይ በጽኑ እምነት መቆም እንዳለበት በማስተማር በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።