ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል








 
 

አር. ሲ. ስፕሮልን በማስታወስ፣ 1939–2017

በስቴፈን ኒኮላስ ታኅሣሥ 14 2017 እ. ኤ. አ.

የነገረ መለኮት ምሁር፣ መጋቢና የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች የሆነው አር. ሲ. ስፕሮል፣ በመተንፈሻ አካል ሕመም ምክንያት የሕክምና ርዳታ ሲደረግለት ቈይቶ በታኅሣሥ 14፣ 2017 እ. ኤ. አ በ78 ዓመቱ ዐርፏል። ዶ/ር ስፕሮል የልጅነት ፍቅረኛውና የ57 ዓመት የትዳር አጋሩ የሆነችውን ቬስታ አንን፣ ሴት ልጁን ሼሪ ስፕሮል ዶሮቲያክንና ባለ ቤቷ ዴኒስ፣ እንዲሁም ወንድ ልጁን አር.ሲ. ስፕሮል ጁኒየርና ባለ ቤቱ ሊሳን ተለይቷል። ስፕሮል ዐሥራ አንድ የልጅ ልጆች (አንድ የልጅ ልጃቸው በሞት የተለየች ሲሆን) እንዲሁም ሰባት የልጅ ልጅ ልጆች አሉት።

አር. ሲ. ስፕሮል ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግል የነገረ መለኮት ምሁር ነበር። ተሐድሷውያኑን የሚያደንቃቸው ስለ መልእክታቸው ይዘት ብቻ ሳይሆን፣ መልእክታቸውን ለሰዎች የሚያስተላልፉበትንም መንገድ ጭምር ነው። እርሱ እንደሚጠራቸው፣ “የጦር ግንባር የነገረ መለኮት ምሁራን” ነበሩ። ብዙዎች የተሐድሶውን ዐምስቱ ሶላዎችን በመጀመሪያ የሰሙት በአር. ሲ. ስፕሮል ትምህርት ነው። አር. ሲ. ስለ ማርቲን ሉተር ሲያስተምር፣ የዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያንን ሐዳሲን በአካል አግኝቶት የሚያውቅ ያህል ነው። አር. ሲ. “ለመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ (ሶላ ስክሪፕቱራ)” አስተምህሮ የነበረው ቊርጠኛነት በመጽሐፍ ቅዱስ ሕጸጽ አልቦነት ዙሪያ የሚናገረው የቺካጎው የእምነት መግለጫን (1978 እ. ኤ. አ.) ለማርቀቅና ለመደገፍ ትልቅ ሚናን እንዲጫወት መርቶታል። በተጨማሪም፣ የዓለም ዐቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጸጽ አልቦነት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል። ለእምነት ብቻ (ሶላ ፊዴ) ወይም በእምነት ብቻ ስለ መጽደቅ አስተምህሮ ከነበረው ቊርጠኛነት የተነሣ፣ በዚሁ አስተምህሮ ዙሪያ በ1994 እ. ኤ. አ. የነበረውን የወንጌላውያንንና የካቶሊኮችን ጥምረት (ECT)ን በጽኑ ተቃውሟል። በኋላ ላይም New Perspective on Paul እና Federal Vision የተባሉትን አስተሳሰቦችን ተቃውሟል። እንደ ተሐድሷውያኑ ሁሉ፣ አር. ሲ. ለርቱዕና ታሪካዊው ክርስትና መሠረታዊና ማዕከላዊ አስተምህሮዎች ሲል ጠንካራ ርምጃዎችን ይወስድ ነበር። የእግዚአብሔር ቃል ሥልጣንና የወንጌሉ ተሟጋችም ነበር። 

በፍልስፍናና በነገረ መለኮት እንደ ሠለጠነ ሰው፣ አር. ሲ. የክላሲካል አፖሎጄቲክስ ደጋፊ ነበር። ጽንስ ማቋረጥን በመቃወም የሚታወቅ የነበረ ሲሆን፣ ውርጃ ምናልባትም የዘመናችን ወሳኙ የሥነ ምግባር ጕዳይ ሳይሆን አይቀርም በማለት ተናግሮ ነበር። ከምንም ነገር በላይ የነገረ መለኮት ሰው ነበር። አስተምህሮተ እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር። በዚህም እግዚአብሔርን ለማወቅ፣ ለማድነቅና እርሱን ለማምለክ መንገድን አግኝቷል። አስተምህሮተ እግዚአብሔር የአር. ሲ. ስፕሮል ሥራና አሻራ የሚሽከረከርበት ማዕከል ነው ማለት ይቻላል፤ ይህም፣ The Holiness of God 1985 እ. ኤ. አ. በተሠኘው ታዋቂ መጽሐፉ ላይ በግልጽ የሚታይ ነው። የእምነት አባት እንደ መሆኑ፣ አጠቃላይ ትውልዱ ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ጋራ እንዲተዋወቅ ረድቷል።

የፒትስበርግ ፍሬ የሆነው ሮበርት ቻርለስ ስፕሮል፣ እ. ኤ. አ. የካቲት 13፣ 1939 ከአባቱ ከሴስል ስፕሮልና ከእናቱ ከሚይር አን (ያርዲስ) ተወለደ። በፒትስበርግ የሒሳብ ሥራ የነበረው የአር. ሲ. አባት፣ በ1942 የገና ዋዜማ ዕለት፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሠራዊቱ ውስጥ አገልግሎቱን ለመጀመር በሞሮኮ ካዛብላንካ ደረሰ። አር. ሲ. የመጀመሪያዎቹን ደብዳቤዎች የጻፋቸው በእናቱ ጕልበት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ለአባቱ በሚላኩት ደብዳቤዎች ግርጌ ላይ “መሳምና ዕቅፍ” የሚል ትርጕም ያላቸውን x እና o የተሠኙትን ሁለት የእንግሊዘኛ ፊደል ቊልፎችን በመጫን አስፍሯል። አር. ሲ. ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱ እስከ መሰናዶ ትምህርቱ ድረስ አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው ከጽሑፍ ይልቅ በስፖርት ሜዳዎች ላይ ነበር። ከስፓርት ብቃቱ የተነሣ በሰሜን ፒትስበርግ በሚገኘው ዌስትሚኒስቴር ኮሌጅ የትምህርት ዕድልን አግኝቶ ነበር። አር. ሲ. ወደ ኮሌጁ የሄደው ሳይለወጥ ቢሆንም፣ በመጀመሪያ የኮሌጅ ዓመቱ ወደ ክርስቶስ መጥቷል።

አር. ሲ. ከኮሌጅ ተመርቆ ሲወጣ አማኝ ብቻ ሳይሆን አስተምህሮ እግዚአብሔርን በተመለከተ “ሁለተኛውን መለወጥ” አግኝቶ ነበር። በኋላ ላይ ይህን ተመክሮ The Holiness of God በሚለው መጽሐፉ የመጀመሪያዎቹ ገጾች ላይ አስፍሮታል። እ. ኤ. አ. በግንቦት 11፣ 1960 አር. ሲ. የልጅነቱ ፍቅረኛ የሆነችውን ቬስታን አግብቷል። እርሷ ገና ከኮሌጅ መመረቋ ሲሆን፣ አር. ሲ. ግን አንድ ዓመት ይቀረው ነበር። እርሷ የሁለተኛ ክፍል፣ እርሱ ደግሞ የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳያት ነበር በርሷ ፍቅር የወደቀው። ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ አር. ሲ.ና ቬስታ በጋራ ነበሩ። 

ከኮሌጅ በኋላ አር. ሲ. በጆን ገርስትነር የቅርብ ክትትል (mentorship) ሥር ወደ ሆነበት ወደ ፒትስበርግ ቲዎሎጂካል ሴሚናሪ አምርቷል። አር. ሲ. አንድ ጊዜ እንዲህ ብሏል፤ “ገርስትነር ባይኖር ኖሮ እጠፋ ነበር።” ከሴሚናሪ ከመመረቁ በፊት፣ በፔንሴልቪኒያ ሊንዶራ ውስጥ ባለ አንድ የፕሪስባይቴራን ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን የመጋቢነት አገልግሎቱን ጀምሮ ነበር። ቤተ ክርስቲያኒቱም የተመሠረተችው በአብዛኛው በአርምኮ የብረት ፋብሪካ ውስጥ የቀን ሠራተኛ ሆነው በሚሠሩ ሃንጋሪያውያን ስደተኞች ነው። ከሴሚናሪ ትምህርቱ በኋላ በፍሪ ዩንቨርሲቲ ኦፍ አምስተርዳም (Free University in Amsterdam) ውስጥ በጂ. ሲ. በርክአወር ሥር የዶክትሬት ጥናቱን ተከታተለ። በክፍል ውስጥ የሚሰጡ ገለጻዎችን በማዳመጥና የመማሪያ መጻሕፍትን በማንበብ ራሱን የደች ቋንቋ አስተማረ። እ. ኤ. አ. በ2016 ሴት ልጁ ሼሪ በደች ቋንቋ የተጻፈውን የፔሪ ማሰንን ልብ ወለድ ያመጣችለት ሲሆን፣ ቋንቋውን በድጋሚ በማንበብ አስደሳች ጊዜን አሳልፏል።

አር. ሲ. በኔዘርላንድ የአንድ ዓመት ቈይታ ካደረገ በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሷል። እ. ኤ. አ. በሰኔ 18 1965 የዩናይትድ ፕሪስባይቴሪያን ቸርች ኢን ዘ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (UPCUSA) አገልጋይ ሆኖ በፕሌዛንት ሂልስ ዩናይትድ ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሾመ። በኋላ ላይ የአገልግሎት ፈቃዱን ወደ ፕሪስባይቴሪያን ቸርች ኢን አሜሪካ (PCA) አዛውሯል። ከዚያ በኋላ በዌስትሚኒስቴር ኮሌጅ (Westminster College 1965–66)፣ በጎርደን ኮሌጅ (Gordon College 1966–68) እና በወቅቱ በፊላደልፊያ የቴምፕል ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ በነበረው ኮንዌል ቴዎሎጂካል ሴሚናሪ (Conwell Theological Seminary) ውስጥ ተከታታይ የሆኑ ሦስት ዐጫጭር የማስተማር ሥራዎችን አግኝቷል። በኮንዌል እያለ፣ ከፊላደልፊያ ውጪ ባለው በኦርላንድ ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሰንበት ትምህርትን ያስተምር ነበር። በመቀጠል በሲንሲናቲ (ኦህዮ) በሚገኘው ኮሌጅ ሂል ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሁለት ዓመታት በመጋቢነት አገልግሏል። 

እ. ኤ. አ. በ1971 አር. ሲ. በምዕራብ ፔንሴልቬንያ ኮረብታማ አከባቢ ላይ በምትገኘው በስታህልስቶውን የሊጎኔር ቫሊ የጥናት ማዕከልን (Ligonier Valley Study Center) መሠረተ። እ. ኤ. አ. በ1984 አገልግሎቱ በኅትመት፣ በሥርጭት (የድምፅና የቪዲዮ)ና በትምህርት አገራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ተደራሲያንን ወደሚያገለግልበት ኦርላንዶ ተዛውሯል። አገልግሎቱ ገና በሊጎኔር ቫሌ ሳለ፣ እ. ኤ. አ. በ1977 የመጀመሪያውን የቴብልቶክ መጽሔት ዕትም አውጥቶ ነበር። የየዕለቱ የጥሞና መጽሔት በአሁኑ ወቅት 100,000 ቅጂዎች የሚሠራጭ ሲሆን፣ አጠቃላይ የአንባቢዎች ብዛትም ከ250,000 በላይ እንደሚሆን ይገመታል። ሊጎኔር እ. ኤ. አ. በ1982 The R.C. Sproul Study Hour የተሠኘ የራዲዮ መርሐ ግብር የጀመረ ሲሆን፣ በመቀጠልም በ1994 Renewing Your Mind የተሠኘውንና ሚሊዮኖችን የደረሰው ዕለታዊ መርሐ ግብርን ማሠራጨት ጀምሯል።

እ. ኤ. አ. ከ1971 እስከ 2017 ድረስ አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ዋና መሪ በነበረበት ወቅት፣ ሊጎኔር ዓመታዊና ብሔራዊ ጉባኤዎችን፣ በመላ አገሪቱ ውስጥ ክልላዊ ጉባኤዎችን፣ ዓለም ዐቀፋዊ ጉባኤዎችን፣ የጥናት ጕዞዎችን ሲያስተናግድ ነበር። እንዲሁም የማስተማሪያ ተከታታይ ቅጾችን፣ መጻሕፍትንና ሌሎች ግብአቶችን አዘጋጅቷል። በተጨማሪም ድረ ገጽን፣ ብሎግን፣ ሬፍኔትንና የሊጎኔር መተግበሪያን ይፋ አድርጓል። በየትኛውም ሳምንታት ውስጥ አገልግሎቱ በዓለም ዙሪያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ይደርሳል። የሊጎኔር ሚኒስትሪስ ቦርድ የተቋሙ የተተኪነት ዕቅድ አካል አድርጎ የሊጎኔርን የመምህራን ኅብረትን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ኅብረቱም ዶ/ር ሲንክሌር ቢ. ፈርጉሰንን፣ ደብሊው. ሮበርት ጎድፍሬይን፣ በርክ ፓርሰንስንና ዴሪክ ደብሊው. ኤች. ቶማስን ያካትታል። ክሪስ ላርሰን የሊጎኔር ሚኒስትሪስ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ ያገለግላል።

ዕውቅ ክርስቲያን መሪ እንደ መሆኑ አር. ሲ ዓለም ዐቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጸጽ አልቦነት ጉባኤ፣ Evangelism Explosion, Prison Fellowship እና Serve International በሚባሉ ማኅበራት ውስጥ የቦርድ አባል ሆኖ አገልግሏል። እ. ኤ. አ. በ1980 አር. ሲ. በነገረ መለኮትና በዕቅብተ እምነት የፕሮፌሰርነትን ማዕረግን ከሪፎርምድ ቴዎሎጂካል ሴሚናሪ (RTS) አግኝቷል። እርሱና ቬስታ በየዓመቱ ለጥቂት ወራት በሚሲሲፒ ወዳለችው ጃክሰን የሚጓዙ ሲሆን በዚያ የተጨናነቀ ጊዜ ውስጥ የሙሉ ጊዜ ኮርስን አስተምሮ ይመለስ ነበር። እ. ኤ. አ. በ1987 ወደ ማዕከላዊ ፍሎሪዳ ከተመለሰ በኋላ፣ አር ቲ ኤስ የኦርላንዶ ካምፓሱን ከፍቷል። አር. ሲ. በጆን ዳየር ትሬምብል ሲኒየር በተሰየመው የስልታዊ ነገረ መለኮት ሊቀ መንበር በመሆን እ. ኤ. አ. ከ1987–1995 ድረስ አገልግሏል። ከዚያም ከ1995–2004 ድረስ በፍሎሪዳ ፎት ላው ዱዳይል በሚገኘው በኖክስ ቲዎሎጂካል ሴሚናሪ (Knox Theological Seminary) ውስጥ የስልታዊ ነገረ መለኮትና የዕቅብተ እምነት ፕሮፌሰር በመሆን አገልግሏል። 

በተጨማሪም፣ አር. ሲ. በድጋሚ ወደ መጋቢነት አገልግሎት ተመልሷል። ትውስታውን ሲያካፍልም፣ “እግዚአብሔር ያልጠበቅሁትን ነገር አድርጓል” በማለት ተናግሯል። ይህም፣ በፍሎሪዳ ሳንፎርድ የሴንት አንድሪው ቻፕል መመሥረቱ ነው። አር. ሲ. በሞተበት ወቅት ከበርክ ፓርሰንስ ጋራ በሴንት አንድሪው በመጋቢነት ያገለግሉ ነበር። እ. ኤ. አ. ጥቅምት 26፣ 2017 በዕብራውያን 2፥1–4 ላይ የተመሠረተውን “እንዲህ ያለ ታላቅ መዳን” በሚል ርእስ የመጨረሻ ስብከቱን ሰብኳል። 

አር. ሲ. ስፕሮል በሞተበት ወቅት፣ እ. ኤ. አ በ2011 በመሠረተው ሪፎርሜሽን ባይብል ኮሌጅ ውስጥ ቻንስለር ነበር። አር. ሲ. የኮሌጁን ስም በማውጣት፣ የትምህርት ሥርዐቱን በመቅረጽ፣ በተሐድሷዊው ትውፊት እግዚአብሔርን በማወቅና በቅድስናው ተማሪዎችን የማስተማርን ተልእኮን በማውጣት የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሆኖ አገልግሏል። በሊጎኔር ካለው የአስተዳደር ቢሮ ውስጥ ሆኖ በመስኮት በስተቀኝ ኮሌጁን፣ በስተግራ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኑን ማየት ይችል ነበር። 

አር. ሲ.፣ The Symbol: An Exposition of the Apostles’ Creed የሚለውን የመጀመሪያ መጽሐፉን እ. ኤ. አ. በ1973 አሳትሟል። በመጽሐፉም ውስጥ የሚከተለውን የአበርክቶት መግለጫ አስቀምጧል፤ “ለሮማውያን የአረማውያን ጣዖት ለሆነችው፣ ለእኔ ግን እግዚአብሔርን የምትፈራ ሚስት ለሆነችው ለቬስታ አበረክተዋለሁ።” የመጀመሪያው መጽሐፉ፣ እንደ ነገረ መለኮት ምሁር በቀጣይነት የሚመጡትን ሥራዎቹን ሲያመለክት፣ አበርክቶቱ ደግሞ የራሱን የአገላለጽ ዘይቤን ያሳያል። እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ፣ ከመቶ በላይ መጻሕፍትን ጽፏል። እነዚህም የልጆችን መጻሕፍት፣ ልብ ወለድ፣ ሦስት ቅጽ ያለው በዌስትሚኒስቴር የእምነት መግለጫ ላይ የተሠራ ማብራሪያ፣ በርከት ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ላይ የተሠሩ ማብራሪያዎችን፣ በብዙ አስተምህሮዎችና የክርስትና ሕይወት ላይ ያተኰሩ መጻሕፍትን ያካትታል። እ. ኤ. አ. በ1984 ከሌሎች ጸሓፊዎች ጋራ Classical Apologetics፣ በ1986፣ Chosen by God እና በ1985 ደግሞ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ታዋቂ ከሆኑት መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውን The Holiness of God አሳትሟል። አር. ሲ. የ Reformation Study Bible ዋና አርታዒ በመሆን አገልግሏል። ከሃያ አራት በላይ ዝማሬዎችን ጽፏል። ጓደኛውና የሙዚቃ አቀናባሪ ከሆነው ከጄፍ ሊፕንኮት ጋራ በአንድነት በመተባበር፣ እ. ኤ. አ. በ2015 Glory to the Holy One እና በ2017 Saints of Zion የሚሉ ሁለት የመዝሙር ሲዲዎችን አውጥቷል። 

የአር. ሲ. መዝሙር የመጻፍ ችሎታ የመነጨው፣ በዕድሜ ዘመኑ ሁሉ ከነበረው የሙዚቃ ፍቅር ነበር። በፕሌዛንት ሂልስ ዩናይትድ ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን የወጣቶች ኳየርና በትምህርት ቤቱ ኳየር ውስጥ ከቬስታ ጋራ ይዘምር ነበር። በተጨማሪም፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ባለ የኅብረ ዜማ ቡድን ውስጥ ወፍራሙን ድምፅ (bass) የሚያዜም አባል ነበር። ፒያኖ ይጫወት የነበረ ሲሆን፣ ዕድሜው ከገፋ በኋላ ደግሞ አዲስ በተመሠረተው ሴንት አንድሪው ኮንሰርቫቶሪ ኦፍ ሚዩሲክ ቫዮሊን መጫወት ተምሯል። አር. ሲ. ሥዕልም ይሥል ነበር። ጎልፍ መጫወትን የሚወድድና በጫወታውም ጎበዝ ነበር። ማደን፣ ፐዝል፣ ማንበብ በተለይም ግለ ታሪኮችን ማንበብ ደስ ያሰኘው ነበር። 

የተካነው መምህር አር. ሲ. ስፕሮል፣ ለቤተ ክርስቲያን ምእመናን አስተምህሮን ማስተማርን ይወድዳል፤ ለዚያም ኖሯል። የማሳቅ ለዛ የነበረው ሲሆን ሁልጊዜም ዐጭር የሚያስቅ ቀልድ አይጠፋውም ነበር። ከአር. ሲ. ጋራ የሚደረጉ ውይይቶች ከጥልቅ ነገረ መለኮታዊ ውይይቶች በቀላሉ ወደ ጎልፍ ስፖርት (ለርሱ ከስፖርት በላይ ነው)ና ቀልዶች ይሸጋገራሉ። በወንጌሉ አእምሮዎች ታድሰው፣ ልቦች ተለውጠውና ኑሮዎች ተቀይረው ማየትን ይናፍቅ ነበር። ነገሮችን ግልጽ የማድረግ አስደናቂ ስጦታ ነበረው። በሙያዊ ቃላት ብዛት አድማጮቹን አያሸማቅቃቸውም፤ እንዲሁም ዝቅ አድርጎ በመመልከትም አይቀርባቸውም። ከባድና ጠንካራ የሆኑ ጕዳዮችን በግልጽና በሚሞግት አጣዳፊነት በጥልቀት ያስተምር ነበር። የስብከት ዘዴ ተማሪዎቹን በምንባቡ ውስጥ ያለውን ድራማ እንዲያገኙና ያንን ድራማ እንዲሰብኩት ያስተምራቸው ነበር። 

አር. ሲ. ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱሱ እግዚአብሔር ጋራ የተገናኘበትን ክሥተት ብዙ ጊዜ ያስታውሰው ነበር። አዲስ ክርስቲያንና በኮሌጅ ውስጥ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሳለ መጽሐፍ ቅዱስን በጕጕት ያነብብ ነበር። ከንባቡ ግልጽ የሆነለት ነገር፣ እግዚአብሔር ነገሮችን በቸልተኛነት የማይመለከት ቁም ነገረኛና ቊርጠኛ አምላክ መሆኑን ነው። መዝሙራቱ፣ የዖዝያን ታሪክ፣ ዘፍጥረት 15፥17፣ የማርያም ዝማሬ፣ ሉቃስ 16፥16–17ና በርግጥም ኢሳይያስ 6– የእነዚህ ምንባባት ድራማ ለመጀመሪያ ጊዜ ካነበባቸው ቅጽበት ጀምሮ አር. ሲ.ን ማርከውት ነበር። 

አር. ሲ. ይህን አስተምሮናል፤ “እግዚአብሔር ቅዱስ ሲሆን እኛ ግን አይደለንም።” በመካከል ያለው አምላክ-ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የርሱ ፍጹም የመታዘዝ ሥራና በመስቀል ላይ የተፈጸመው የማስተሰረያ ሞቱ ነው። ይህ የአር. ሲ. ስፕሮል መልእክትና አሻራ ነው (1939–2017 እ. ኤ. አ.)።