በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ጸሎት ያለው ስፍራ

16 ሐምሌ 2026

እውነተኛ ንስሓ ምን ይመስላል?

20 ሐምሌ 2026

በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ጸሎት ያለው ስፍራ

16 ሐምሌ 2026

እውነተኛ ንስሓ ምን ይመስላል?

20 ሐምሌ 2026

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔር በግ

ይህ “የእግዚአብሔር በግ” የሚለው ሐሳብ፣ በቤዛነት ታሪክ ሁሉ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጥ መስመር ነው። ይህም ሐሳብ እግዚአብሔር አብርሃምን ወደ ሞሪያ ተራራ ሄዶ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ከጠራበት ከዘፍጥረት 22 የሚጀምር ነው። አብርሃም ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ያንኑ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ነበር፤ ነገር ግን አብርሃም ይስሐቅን በመሠዊያው ላይ ካሰረውና ቢላውን ወደ ልቡ ለመሰንዘር በተዘጋጀበት በዚያ የመጨረሻ ቅጽበት እግዚአብሔር፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” በማለት አስቆመው (ዘፍጥረት 22፥12)። ከዚያም ከአብርሃም ጀርባ አንድ ድምፅ ተሰማ፤ ዘወር ሲልም ቀንዶቹ በቍጥቋጦ ውስጥ የተያዙ አንድ አውራ በግ አየ። እግዚአብሔር በአብርሃም ልጅ ፈንታ የሚቀርብ ምትክ መሥዋዕት የሚሆን በግን አዘጋጀ። በርግጥ አብርሃም በይስሐቅ ፈንታ አግኝቶ ያቀረበው አውራ በግ፣ የኀጢአት ማስተስርያ መሥዋዕት ስለ መሆኑ በዘፍጥረት 22 ላይ በግልጽ የተጠቀሰ ነገር የለም። ሆኖም ግን፣ ያ መሥዋዕት ምትካዊ መሥዋዕት ነበር። ይህም ለክርስቶስ የስርየት ሞት መሠረት የሆነው ሐሳብ ነው። ኢየሱስ የእኛ ምትክ ሆኖ ይሠራል፤ እግዚአብሔርም በእኛ ላይ ሊያፈስ የነበረውን በኀጢአታችን ምክንያት የመጣውን ቍጣውን በእኛ ፈንታ በርሱ ላይ ያፈስሰዋል። በመሆኑም እግዚአብሔር የራሱን በግ ያዘጋጃል፤ የዚያንም ምትክ ሕይወት ይቀበላል።

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ “የእግዚአብሔር በግ” የሚለው ሐሳብ በፋሲካ ውስጥ በምሳሌነት አስቀድሞ ታይቷል። እግዚአብሔር የመጨረሻውን መቅሠፍት በግብጻውያን ላይ ለማምጣት፣ ይኸውም የፈርዖንን ዐልጋ ወራሽ ጨምሮ የግብጻውያንን በኵር ወንዶች ሁሉ ለመግደል በተዘጋጀ ጊዜ፣ ሕዝቡ እስራኤል ነውር የሌለባቸውን በጎች እንዲያርዱና ደማቸውንም በበራቸው መቃኖች ላይ እንዲቀቡ አዘዛቸው። እግዚአብሔርም በበሩ መቃኖች ላይ የበጎቹን ደም ባየበት ቤቶች ሁሉ ላይ ዐልፎ እንደሚሄድ ቃል ገባ (ዘፀአት 12፥3-13)። የእነዚያ በጎች ደም የእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር ቍጣ እንዲተርፉ እንዳደረገ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በግም ሕዝቡን ለኀጢአታቸው ይገባ ከነበረው ቅጣት ዋጅቷቸዋል።

በዘፍጥረት 22፣ በዘፀአት 12 እና በሌሎችም የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን ምስላዊ መግለጫዎችን ስንመለከት፣ “የእግዚአብሔር በግ” የሚለው መጠሪያ የሐዋርያው ዮሐንስ የፈጠራ ውጤት ነው ማለት ሞኝነት ነው። የመጥምቁ ዮሐንስ ንግግር በወቅቱ የነበረውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ ነበር።

በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ “የእግዚአብሔር በግ”፣ “የእግዚአብሔር ልጅ”፣ “መሲሕ”፣ “የሰው ልጅ” እና የመሳሰሉት ለኢየሱስ የተሰጡ ታላላቅ መጠሪያዎችና ማዕረጎች በብዛት ቢጠቀሱም፣ መጥምቁ ዮሐንስ፣ እንድርያስ፣ ናትናኤልም ሆኑ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ማናቸውም የእነዚህን መጠሪያዎች ትርጕም ሙሉ በሙሉ የተረዱ አይመስለኝም። “እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” በማለት የመሰከረው መጥምቁ ዮሐንስ፣ በኋላ ላይ ታስሮ በነበረበት ወቅት ወደ ኢየሱስ መልእክተኞችን በመላክ፣ “የሚመጣው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” በማለት ጠይቋል (ሉቃስ 7፥20)። ይህ ጥያቄ የሚያሳየው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ማንነት ያን ያህል ታላቅ ምስክርነትን ቢሰጥም፣ ማንነቱን ግን ሙሉ በሙሉ እንዳልተረዳው ነው። ችግሩ ዮሐንስ የራሱ የሆነ ግምትና ፍላጎት ስለ ነበረው ነው። እንደ ማንኛውም ሰው፣ የእግዚአብሔር በግ መጥቶ ሮማውያንን ጠራርጎ ያስወጣል ብሎ ይጠብቅ ነበር። ኢየሱስን ወንጌልን ለመስበክ ብቻ ሲዘዋወር ባየው ጊዜም ግራ ተጋባ።

ኢየሱስ ለዮሐንስ መልእክተኞች እንዲህ አላቸው፦

“ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቈሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤” (ሉቃስ 7፥22)

ኢየሱስ ግራ ለተጋባው ዮሐንስ ማንነቱን ለማረጋገጥ ተአምራቱን እንደ ማስረጃ አቀረበ። በተጨማሪም በኢሳይያስ 61፥1-2ሀ ላይ የሚገኘውን መሲሓዊ ትንቢትን በመጥቀስ እንዲህ አለ፦

“የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤

ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣

       እግዚአብሔር ቀብቶኛልና።

ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣

ለምርኮኞች ነጻነትን፣

ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።

የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣

የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣”

ኢየሱስ እንዲህ እየተናገረ ያለ ይመስል ነበር፤ “ዮሐንስ ሆይ፣ መጽሐፍ ቅዱስህን በሚገባ አጥንተህ ቢሆን ኖሮ፣ ‘የሚመጣው አንተ ነህ ወይ?’ ብለህ አትጠይቅም ነበር። ሌላ ሰው መጠበቅም አያስፈልግህም ነበር። በመጀመሪያው ምስክርነትህ ላይ ትክክል ነበርህ፤ የእግዚአብሔር በግ እኔ ነኝ።”

ጴጥሮስም ቢሆን በፊልጶስ ቂሳርያ ያንን ታላቅ ምስክርነት በሰጠበት ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ ግራ ተጋብቶ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ማን እንደ ሆነ እንደሚያስቡት ለጠየቃቸው ጥያቄ ጴጥሮስ፣ “አንተ ክርስቶስ፣ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት መልሷል (ማቴዎስ 16፥16)። ኢየሱስም ይህ ምስክርነት ትክክል መሆኑን አረጋገጠ፤ ማንነቱንም በመረዳቱ ጴጥሮስን “ብፁዕ ነህ” ብሎታል። ነገር ግን ከዚያ በኋላ ወዲያውኑ ኢየሱስ መከራን ለመቀበልና ለመሞት ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ እንዳለበት ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው፣ ጴጥሮስ ገሠጸውና “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” አለው (ማቴዎስ 16፥22ለ)። ጴጥሮስ በአንድ በኩል ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን መሰከረ፤ በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ መሲሕ መሆኑ ምን ማለት እንደ ሆነ ሙሉ በሙሉ አለመረዳቱን ገለጠ።

እኛም ብንሆን ለእንዲህ ዐይነቱ ግራ መጋባት የተጋለጥን ነን። መስቀሉን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱንና በጴንጠቆስጤ ቀን የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስን ግምት ውስጥ በማስገባት አጠቃላዩን ሥዕል ስንመለከት ብቻ ነው፣ “እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” በማለት የእግዚአብሔር መልእክተኛ ካወጀው ቃል ጀርባ እግዚአብሔር ሲያስተላልፍ የነበረውን ጥልቅና የበለጸገ እውነት ማስተዋል የምንጀምረው።


ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው

አር. ሲ. ስፕሮል

አር. ሲ. ስፕሮል

ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች ሲሆን በፍሎሪዳ ሳንፎርድ በሚገኘው በሴንት አንድሪው ቻፕል ውስጥ በስብከትና በትምህርት የሚያገለግል የመጀመሪያው አገልጋይ፣ የሪፎርሜሽን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የቴብልቶክ መጽሔት ዋና አርታዒ ነበር። Renewing Your Mind የተሠኘው የራዲዮ ፕሮግራሙ በየዕለቱ በዓለም ላይ በሚገኙ በመቶዎች በሚቈጠሩ የራዲዮ ጣቢያዎችና በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት አሁንም ድረስ ይደመጣል። The Holiness of God, Chosen by God እና Everyone’s a Theologian የሚሉትን ጨምሮ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጸጽ አልቦነት በመከላከልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በቃሉ ላይ በጽኑ እምነት መቆም እንዳለበት በማስተማር በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።