የእምነት መግለጫችን

ሊጎኔር ሚኒስትሪስ የጥንት የእምነት መግለጫዎችን ይቀበላል። እነዚህም፣ የሐዋርያት የእምነት መግለጫ፣ የኒቂያ የእምነት መግለጫና የቃልኬዶን የእምነት መግለጫ ናቸው። በተሐድሶው ዐምስቱ ሶላዎች (ብቻዎች)ና በታሪካዊ የተሐድሶ የሃይማኖት መግለጫዎች (የዌስት ሚኒስቴር የእምነት መግለጫ፣ ስሪ ፎርምስ ኦፍ ዩኒቲ /የቤልጂክ፣ የሄድልበርግና የዶርት ጉባኤን ይመለከታል/፣ የ1689 የለንደን ባፕቲስት የእምነት መግለጫ ) የጋራ ስምምነት የተገለጠውን የታሪካዊ ክርስትና እምነትን እናጸናለን።

መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ በአጠቃላይ የማይሳሳት፣ ሕጸጽ አልቦና እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነ ቃል ነው። ሙሉ የእግዚአብሔር ሥልጣንን የተሸከመ እንድንገዛለት የሚያስገድደን መለኮታዊ መገለጥ ነው። 

ሥላሴ

በግጻዌ መለኮት ፍጹም አምላክ የሆኑ ሦስት የተለያዩ አካላት (አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ) አንድነትን እናገኛለን። እነዚህም ሦስት አካላት አንድ እግዚአብሔር ሲሆኑ አንድ ዐይነት ባሕርይ፣ እኩል ሥልጣንና ክብር አላቸው።

እግዚአብሔር

እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ በማንነቱ፣ በጥበቡ፣ በኀይሉ፣ በቅድስናው፣ በፍትሑ፣ በመልካምነቱና በእውነት ኢ-ውሱን የሆነ፣ ዘላለማዊና የማይለወጥ ነው። እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ሁሉን የሚያውቅ፣ ሁሉን የሚችልና በሁሉ ስፍራ የሚገኝ ሲሆን በዕውቀቱ የሚማርና የሚያድግ አይደለም። 

ኢየሱስ ክርስቶስ

ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክና እውነተኛ ሰው ሲሆን ሁለት ባሕርያት ያለ መደባለቅ፣ ያለመነጣጠልና ያለመከፋፈል በአንድ መለኮታዊ አካል ውስጥ አሉት። እያንዳንዱ ባሕርይ የገዛ ራሱን ባሕርያትን ይጠብቃል። በተሠግዎ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በመካከላችን ፍጹም ሕይወትን በመኖር፣ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ ሞቶ ተቀብሯል። በሦስተኛው ቀን ከሙታን በመነሣት ወደ ሰማይ ያረገ ሲሆን በክብርና በፍርድ በድጋሚ ተመልሶ ይመጣል። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ብቸኛው መካከለኛ እርሱ ነው። 

መንፈስ ቅዱስ

መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋራ አንድ ዐይነት ባሕርይ አለው። እርሱ ከአብና ከወልድ ከዘላለም የወጣ ሲሆን፣ በአማኞች ልብ ውስጥ ያድራል፤ ብቻውን (monergistically) ዳግም ልደታቸውን የሚፈጽም ሲሆን ቅድስናቸውን ደግሞ በጋራ (synergistically) ይፈጽማል።

ፍጥረት

እግዚአብሔር በኀያል ቃሉ ሰማይንና ምድርን ደግሞም በውስጡ ያሉትን ሁሉ ከምንም ፈጥሯል። በተጨማሪም፣ በርሱ ቅዱስ፣ ጠቢብና ኀያል መግቦት መሠረት ፍጥረቱን ሁሉና ድርጊታቸውን ሁሉ ይጠብቃል፤ ይመራልም። 

ሰው

እግዚአብሔር ሌሎች ፍጥረታትን ከፈጠረ በኋላ፣ በመልኩና በምሳሌው ወንድና ሴት አድርጎ ሰውን ፈጥሯል። ነገር ግን አዳም ኀጢአትን ከማድረጉና በሚያስደነግጥ ሁኔታ ኀላፊነቱን ከመፈጸም በመውደቁ እርሱና ዘሩ ወደ ምግባር ውድቀትና አለመቻል ሁኔታ ውስጥ በመግባት ከፈጣሪያቸው ተለይተዋል። ስለዚህም፣ የኀጢአታቸው ቅጣት ሆኖ ሞት ይገባቸዋል።

ስርየት

ሁሉም ኀጢአትን ስላደረጉ ሰው ከእግዚአብሔር ጋራ ይታረቅ ዘንድ ስርየት መፈጸም አለበት። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባከናወነው ምትካዊ የስርየት ሞት አማካይነት ለሕዝቡ ሙሉ ስርየትን ፈጽሟል። የርሱን ጽድቅ ለሁሉም አማኞች የሚቈጥርላቸው ሲሆን ንስሓ ለሚገባና ለድነት በርሱ ብቻ ለሚታመን ሁሉ ሙሉ መቤዠትን ያረጋግጥለታል። 

ሕጉ

የምግባር ሕግ፣ የእግዚአብሔርን የማይለወጥ ባሕርይ ፍጹም በሆነ መልኩ ያንጸባርቃል። ደግሞም ሁሉንም ሰዎች ማለትም አማኞችንም ሆነ አላማኞችን ለዘላለም እንዲታዘዙት የሚያስገድድ ነው። 

ቤተ ክርስቲያን

ክርስቶስ የምትታይ ቤተ ክርስቲያንን መሥርቷል። ይህች ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን አመራር ሥር የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐቶችን በመፈጸምና የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽን በመተግበር እንድትኖር ተጠርታለች።

ክርስትናና ባህል

የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣንንና የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት የሚመሰክሩትን፣ ደግሞም ለሰውና ለአከባቢው ደኅንነት ሲሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ማኅበራዊና ባህላዊ እንድምታዎችን ለመፈጸም ቊርጠኛ የሆኑ የክርስቲያናዊ ድርጅቶችንና ተቋማትን ሥራ ሊጎኔር ይደግፋል። ሊጎኔር በተለይም ገና በማሕጸን ሳሉ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ የሰው ልጆችን ግድያና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ የሥርዐተ ጾታ፣ የወሲባዊ ግንኙነትና የጋብቻ ትርጓሜዎችን የሚያወግዙ ተቋማትን ይደግፋል።

በተጨማሪም የሊጎኔር የነገረ ክርስቶስ የእምነት መግለጫን ይመልከቱ።