
በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ጸሎት ያለው ስፍራ
16 ሐምሌ 2026ማስተስረይ (Expiation) እና ቍጣ ማብረድ (Propitiation) ምን ማለት ናቸው?
ስለ ክርስቶስ ምትካዊ የስርየት ሞት ስንነጋገር፣ ሁለት ሙያዊ ቃላት ደጋግመው ይመጣሉ። እነርሱም፣ ማስተስረይ እና ቍጣ ማብረድ ናቸው። እነዚህ ቃላት አንድን የግሪክ ቃል ለመተርጐም የትኛው ጥቅም ላይ መዋል አለበት በሚል የተለያዩ ክርክሮችን ያስነሣሉ። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጕሞች አንዱን ሲጠቀሙ፣ ሌሎቹ ደግሞ ሌላኛውን ይጠቀማሉ። በማስተስረይ እና በቍጣ ማብረድ መካከል ያለውን ልዩነት እንዳስረዳ ብዙ ጊዜ እጠየቃለሁ። ችግሩ ግን እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢኖሩም፣ በዕለት ተ’ለት ንግግራችን ውስጥ ስለማንጠቀምባቸው በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ዐውድ ውስጥ ምን እያስተላለፉ እንደ ሆነ በትክክል ርግጠኞች አይደለንም። እነዚህን ቃላት የምናነጻጽርበት የቋንቋ ልምድ ያጥረናል።
ማስተስረይ እና ቍጣ ማብረድ
እስቲ እነዚህ ቃላት ምን ማለት እንደ ሆኑ እናስብ፤ በ“ማስተስረይ” እንጀምር። ማስተስረይ የሚለው የእንግሊዘኛው ቃል Expiation (ኤክስፒየሽን) ሲሆን “ኤክስ” [Ex] የሚለው የፊት ቅጥያ “ከ… ውስጥ” ወይም “ከ… ዘንድ” [Out of / From] የሚል ትርጕም አለው። ስለዚህ ኤክስፒየሽን አንድን ነገር ከማስወገድ ወይም ከማራቅ ጋራ የተያያዘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጽ፣ ቅጣትን በመክፈል ወይም የስርየት መሥዋዕትን በማቅረብ ጥፋተኛነትንና በደለኛነትን ማስወገድ ማለት ነው። በአንጻሩ፣ ቍጣ ማብረድ ከማስተስረዩ ግብ ጋራ የተያያዘ ነው።ቍጣ ማብረድን የሚገልጸው የእንግሊዝኛ ቃል Propitiation (ፕሮፒሽየሽን) የሚል ሲሆን “ፕሮ” [Pro] የሚለው የፊት ቅጥያ “ለ…” [For] የሚል ትርጕም አለው። ስለዚህ ቍጣ ማብረድ፣ በእግዚአብሔር አመለካከት ላይ ለውጥን ያመጣል። ይህም ማለት ከእኛ ጋራ ከነበረው ጠላትነት ተመልሶ ለእኛ እንዲወግን ያደርገዋል። በዚህ ቍጣ የማብረድ ሂደት አማካይነት፣ በድጋሚ ከርሱ ጋራ ወዳለ ኅብረት እንገባለን፤ በፊቱም ተቀባይነትን እናገኛለን።
በአንድ በኩል፣ቍጣ ማብረድ እግዚአብሔርን ከማርካት [Appeased] ጋራ የተያያዘ ነው። “ማርካት/ማብረድ” የሚለው ቃል በወታደራዊና በፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ እንዴት እንደሚሠራ እናውቃለን። “የማብረድ ፖለቲካ” የሚባለውን እናስብ፤ ይህም ለምሳሌ አንድ ግፈኛና ዓለምን ለመውረር የሚገሠግሥ ኀይል ቢነሣ፣ የርሱን አስፈሪ ቍጣ ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ከቼኮዝሎቫኪያ ላይ “ሱዴተንላንድን” ወይም መሰል ግዛቶችን አሳልፎ የመስጠት ፍልስፍና ነው። አገራችሁ ገብቶ እንዳያጠፋችሁ በሚያረካው ነገር ቍጣውን ለማብረድ ትሞክራላችሁ። ይህ ጤናማ ያልሆነ የማብረድ መገለጫ ነው። ነገር ግን እናንተ ተቈጥታችሁ ወይም ተበድላችሁ ቢሆንና እኔ ቍጣችሁን ባበርድ፣ ያን ጊዜ በድጋሚ በፊታችሁ ተቀባይነትን አገኛለሁ፤ ችግሩም ይወገዳል።
አንዱ የግሪክ ቃል አንዳንድ ጊዜ ማስተስረይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቍጣ ማብረድ ተብሎ ይተረጐማል። ሆኖም በቃላቱ መካከል መጠነኛ ልዩነት አለ። ማስተስረይ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው አመለካከት እንዲለወጥ የሚያደርገው “ተግባር” ነው። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገው ነገር ነው፤ የክርስቶስ የማስተስረይ ሥራ ውጤት ደግሞ ቍጣ ማብረድ ነው፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ቍጣ መመለሱ ነው። ልዩነቱ፣ በተከፈለው ቤዛና ቤዛውን በተቀበለው አካል አመለካከት መካከል ካለው ልዩነት ጋራ ተመሳሳይ ነው።
የክርስቶስ ሥራ ቍጣን የማብረድ ድርጊት ነበር
ማስተስረይ እና ቍጣ ማብረድ በአንድ ላይ ሆነው ቍጣን የማብረድ ድርጊትን ያመለክታሉ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሠራው ሥራ የእግዚአብሔርን ቍጣ ለማብረድ ነበር። ይህ የእግዚአብሔርን ቍጣ የማብረድ ሐሳብ የዘመናዊ ነገረ መለኮት ምሁራንን ቍጣ ለማብረድ ግን ምንም አላገዘም። እንዲያውም የእግዚአብሔርን ቍጣ ማብረድን በተመለከተ በሚነሣው ሐሳብ ላይ በጣም ይቈጣሉ። እግዚአብሔር ሊበርድ ወይም ከቍጣ ሊመለስ ይገባዋል ማለት፣ ለእግዚአብሔር ክብር የማይመጥን አድርገው ይቈጥሩታል። እኛ የእግዚአብሔርን ቍጣ የምንረዳበት መንገድን በተመለከተ በጣም መጠንቀቅ አለብን፤ ነገር ግን ላሳስባችሁ የምፈልገው፣ የእግዚአብሔርን ቍጣ የማብረድ ፅንሰ ሐሳብ በነገረ መለኮት ውስጥ ተቀዳሚ ያልሆነ በዳር የሚገኝ ሐሳብ ሳይሆን፣ የደኅንነት ዋና ማዕከል መሆኑን ነው።
ደኅንነት ምንድን ነው?
አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፦ ደኅንነት የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? ይህን ቃል በፍጥነት ለማብራራት መሞከር ራስ ምታት ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም፣ “ደኅንነት” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ ሰባ በሚጠጉ ልዩ ልዩ መንገዶች ጥቅም ላይ ውሏል። አንድ ሰው በጦርነት ውስጥ ከሚመጣ ሽንፈት ቢተርፍ ደኅንነትን አግኝቷል። አንድ ሰው ለሕይወት አሥጊ ከሆነ በሽታ ቢድን ደኅንነትን አግኝቷል። አንድ ሰው እየደረቁ ያሉ ተክሎቹ አገግመው ለምለም ቢሆኑለት፣ ተክሎቹ ድነዋል ይባላል። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አነጋገር ነው፤ ከእኛም የዕለት ተ’ለት ንግግር የተለየ አይደለም። “ገንዘብ አዳንኩ [አጠራቀምኩ]” እንላለን። አንድ ቦክሰኛ በመጨረሻው ሰዓት በደውል ድምፅ ከሽንፈት ቢተርፍ “በደውል ዳነ” ይባላል፤ ይህ ማለት ግን ወደ ዘላለማዊቷ የእግዚአብሔር መንግሥት ገባ ማለት ሳይሆን፣ ራሱን ስቶ በዳኛው ተቈጥሮበት ከመሸነፍ ተረፈ ማለት ነው። በዐጭሩ፣ ግልጽ ከሆነና በፊታችን ካለ አሁናዊ አደጋ የመትረፍ ማንኛውም አጋጣሚ “ደኅንነት” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።
ስለ ደኅንነት በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድ ስንናገር፣ በዋናነት ከምን እንደ ዳንን መግለጽ አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ተሰሎንቄ 1፥10 ላይ፣ “ከሚመጣውም ቍጣ የሚያድነንን ኢየሱስን” በማለት ይህንኑ ይገልጽልናል። በመሠረቱ ኢየሱስ የሞተው ከእግዚአብሔር ቍጣ ሊያድነን ነው። ይህ ካልገባን በቀር የናዝሬቱ ኢየሱስን ትምህርትና ስብከት ልንረዳ አንችልም። ምክንያቱም፣ እርሱ መላው ዓለም አንድ ቀን በመለኮታዊ ፍርድ ሥር እንደሚወድቅ ሰዎችን ዘወትር ያስጠነቅቅ ነበር። ስለ ፍርድ ከሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች ጥቂቶቹ እነሆ፦ “እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” (ማቴዎስ 5፥22)፤ “እኔ እላችኋለሁ፤ ሰዎች ለሚናገሩት ለእያንዳንዱ ከንቱ ቃል በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” (ማቴዎስ 12፥36)፤ እና “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤ እነሆም፣ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ” (ማቴዎስ 12፥41)። የኢየሱስ ነገረ መለኮት “የክሪሲስ ነገረ መለኮት” ነበር። “ክሪሲስ” የሚለው የግሪክ ቃል “ፍርድ” ማለት ነው። ኢየሱስ የሰበከው ክሪሲስ፣ በዓለም ላይ ስለሚመጣው የማይቀረው ፍርድ ነበር፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር ቍጣውን ባልተዋጁት፣ እርሱን በማይፈሩትና ንስሓ ባልገቡት ላይ ያፈስሳል። ከዚህ ቍጣ ለማምለጥ ያለው ብቸኛ ተስፋ በክርስቶስ ስርየት መሸፈን ብቻ ነው።
ስለዚህ፣ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የፈጸመው ታላቅ ድልና ስኬት፣ በመሥዋዕቱ ባንሸፈን ኖሮ በእኛ ላይ የሚነድደውን የእግዚአብሔርን ቍጣ ማብረዱ ነው። ስለሆነም፣ ማንም ሰው ቍጣን ማብረድ ወይም ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቍጣ የማርካቱን ሐሳብ ቢቃወም፣ ንቁ ሁኑ፤ ምክንያቱም ወንጌሉ አደጋ ላይ ነው። ይህ የደኅንነትን ዋና ማዕከል የሚመለከት ጕዳይ ነው። ይኸውም በስርየት የተሸፈንን ሰዎች እንደ መሆናችን መጠን፣ ማንኛውም ሰው ሊጋፈጠው ከሚችለው ከታላቁ አደጋ ተዋጅተናል። በቍጣ በተሞላው በቅዱሱ እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነገር ነው። ነገር ግን ኀጢአታቸው በተከፈለላቸው ሰዎች ላይ የሚቀር ምንም ቍጣ የለም። የደኅንነትም ዋናው ነገር ይኸው ነው።
ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው


