የማንደራደርባቸው አቋሞች
በዙሪያችን ያለው ዓለም ሁልጊዜ የሚለወጥ ቢሆንም፣ ታሪካዊው የክርስትና እምነትን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ይበልጥ እንዲታወቅና እንዲሰፋ ለማድረግ እንተጋለን። ይህን ከግብ ለማድረስም፣ ሊጎኔር ሚኒስትሪስ እነዚህን ዐሥር አቋሞችን አበጅቷል፤ በዐደራ የተሰጠንን ተልእኮ በመፈጸም ታማኝ ሆኖ ለመጽናት በእግዚአብሔር ጸጋ እንደገፋለን።
1. ለታሪካዊው የክርስትና እምነት ወጥና ጽኑ የሆነ ቍርጠኛነትን መያዝ
በሚለዋወጡ ጊዜያት ውስጥ አንለወጥም። ይልቁንም፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣንና ከክርስቶስ መስቀል በቂነት ጥንካሬን እናገኛለን። እጅግ ብዙ ሰዎች በቤተ ሰባቸው፣ በቤተ ክርስቲያናቸው፣ በሙያቸው፣ በማኅበረ ሰባቸውና በአገራቸው እንዲለመልሙና እንዲያድጉ ለመርዳት ከታሪካዊው የክርስትና እምነት የአስተምህሮ ብልጥግና እንጠቀማለን። ዐላማችን፣ ክርስቲያኖች በእምነት እንዲኖሩና ከዓለማዊነት (secularism)፣ ከሐሰተኛ ሃይማኖቶችና አክራሪ ከሆነው ከሐዲነት የሚሰነዘርባቸውን ተግዳሮቶችን መቋቋም እንዲችሉ ማድረግ ነው። ለሁሉም መከራዎች ግድ የሚለን ቢሆንም፣ በተለየ መልኩ ለዘላለማዊ መከራ ይበልጥ ግድ ይለናል፤ ደግሞም፣ የታላቁ ተልእኮ ደቀ መዝሙር የማድረግ ታላቅ ተነሣሥቶት ሌሎችን የመድረስ ሁሉንም ተግባራቶቻችንን የሚገፋ ኀይል ነው።
2. ትኩረት ነገረ መለኮት ላይ ብቻ
ለሰዎች ማድረግ የምንችለው እጅግ የላቀው የፍቅር ተግባር እውነቱን መስጠት ነው። ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል፣ ትክክለኛ አስተሳሰብ ትክክለኛ ኑሮን ይቀድማል በማለት ተናግሯል። ስለ እግዚአብሔር የምናስበው ነገር ማንነታችንን ይቀርጻል፤ መሠረታዊ ወደ ሆኑት እምነቶቻችን ዘልቆ የሚገባና እሴቶቻችንን፣ ግባችንና ውሳኔዎቻችንን የሚቀርጽ ነው። ነገረ መለኮት ማለት፣ እናመልከውና በርሱም ደስ እንሰኝ ዘንድ የእግዚአብሔርን ማንነት ማወቅ ነው። በእግዚአብሔር ጸጋ ለሁሉም ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ጥቅም ሲባል ታማኝና ፍሬያማ ወደ ሆነው ኑሮ ለሚመራው እውነት ያለንን የማይናወጥ ቊርጠኛነት ጠብቀን እንቀጥላለን።
3. በድምፅና በተንቀሳቃሽ ምስል (ኦዲዮና ቪዲዮ) ሥራዎች ላይ መዋዕለ ነዋይን ማፍሰስ
በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ክርስቲያናዊ ትምህርትን በተመለከተ ሁልጊዜም ፈር ቀዳጆች ነን። ዛሬ ላይ ስሕተት በብዛት በሞላበት ገበያ ውስጥ ታማኝ የሆኑ ትምህርቶችን በቀጣይነት ለማቅረብ የስቱዲዮአችንን ዐቅም በማሳደግ፣ ተጨማሪ ክህሎት ያላቸው ባለ ሙያዎችን በመቀበል፣ የክርስቲያናዊ አስተምህሮ ቤተ መጻሕፍታችንን ይበልጥ በማጠንከር ላይ እንገኛለን። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ወቅታዊውን የድምፅ ይዘት ያላቸው ፕሮግራሞች ሥርጭት ማንሰራራትን ለመጠቀም በአዳዲስ ፖድካስቶችና የራዲዮ ሥርጭቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መዋዕለ ነዋያችንን እያፈሰስን እንገኛለን።
4. ለሁሉም ክርስቲያናዊ ሕይወት ደረጃ የሚሆኑ ጽሑፎችን ማሳተም
በመላው ዓለም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት በጣም ዝቅተኛ ነው። የደቀ መዝሙርነትን መመዘኛ የሚናገሩት ሥነ ጽሑፎቻችን የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ያስተላልፋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛችን፣ ወርኀዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መጽሔቶች፣ ታማኝ በሆኑ ሰዎች የሚጻፉ መጻሕፍት፣ የበይነ መረብ የመጣጥፎች ቋትና የመሳሰሉት ሰዎች እግዚአብሔር ማን እንደ ሆነና እንዴት እንዲኖሩ እንደሚፈልግ ወደ ማወቅ ሲመጡ፣ በቀዳሚነት ከሚመርጧቸው ግብአቶች መካከል ሆነው ይቀጥላሉ።
5. ክርስቲያኖችን በማኅበረ ሰብ መሰብሰብ
ብረት ብረትን እንደሚስል፣ ክርስቲያኖችም በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ አእምሮአቸውና ኀይላቸው እግዚአብሔርን ለመውደድ እርስ በርስ መበረታታት አለባቸው። ክርስቲያኖችን በአካል ለሚገናኙባቸው ኮንፍረንሶች፣ መቀራረብን ለሚያመጡ ሥልጠናዎች፣ በኦርላንዶ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጃችን ለሚሰጡ ጠንካራ የትምህርት መርሐ ግብሮች አማኞችን እንሰበስባለን። ምክንያቱም፣ ማንም ተነጥሎ እንዲያድግ አልተፈጠረም። በማኅበረ ሰብ ውስጥ ስናድግ እግዚአብሔርን ይበልጥ እንወድዳለን፤ እናገለግላለን።
6. አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም
ጳውሎስ ደብዳቤዎቹን ወደ ተደራስያኑ እንዲደርሱ ለማድረግ የሮም መንገዶችን ተጠቅሟል። ማርቲን ሉተር የጉተንበርግን የማተሚያ አዲስ ግኝትን ተገልግሎበታል። እንዲሁም ዶ/ር ስፕሮል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በአግባብ በመጠቀም፣ ርቀቶችና የቋንቋ መሰናክሎች ሊወገዱ የሚችሉ መሆናቸውን አስተውሏል። በእያንዳንዱ ሰው እጅ ላይ የሞባይል ስልኮች ባሉበት በዚህ ዘመን፣ የአገልግሎታችንን ተደራሽነት ለማስፋት በኢንተርኔት አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኵረት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።
7. ዐውድ በጠበቀ አቀራረብ ለአከባቢያዊ አስፈልጎቶች ምላሽ መስጠት
በዓለም ዙሪያ ሁሉ የእግዚአብሔር እውነት ራብ ስላለ፣ ሊጎኔር የእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ አገልግሎት አይደለም። በዓለም ዙሪያ ካሉ ክርስቲያኖች ጋራ እንገናኛለን፤ ልዩ ፍላጎታቸውንም እንረዳለን፤ ቤተ ሰቦችን፣ አብያተ ክርስቲያናትንና ትምህርት ቤቶችን በክርስቶስ እንዲያድጉ ለመርዳት፣ የደቀ መዝሙርነት ትምህርቶችን ወደ ብዙ ቋንቋዎችና አገሮች እናሠራጫለን።
8. ታማኝ የሆኑ ዓለም ዐቀፋዊ አጋሮችን ማግኘት
ማንኛውም አገልግሎት ሥራውን ብቻውን ሊያከናውን አይችልም። ተመሳሳይ ራእይ ያላቸውን በተለያየ ቦታ ላይ ሆነው የተለያዩ ሕዝቦችን የሚያገለግሉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ሚስዮናውያንና ድርጅቶችን እንፈልጋለን። ማንነታችንን በሚገባ እናውቃለን፤ ደግሞም ባለ ራእይ ለሆኑ ለጋሾቻችን ምስጋና ይግባቸውና ታማኝ የሆኑ የደቀ መዝሙርነት ግብአቶችን ሰዎች ባሉበት የትኛውም ስፍራ ላይ ለማቅረብ በተለየ መልኩ ብቃቱ አለን።
9. መጋቢዎችና መሪዎችን ማስታጠቅ
የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰብኩ ሰዎችን መጥረቢያ ስለታማ ለማድረግ ርዳታ እያደረግን ነው። እነዚህ ሰዎች ስልታዊ የሆነ መታደስን የማግኘት አስፈልጎት አላቸው፤ ይህንም የምናደርገው በስብከት ሴሚናሮችና ኮንፍረንሶች፣ እንዲሁም ደግሞ ለእነርሱ ብቻ በተዘጋጁ የክርስቲያናዊ ዕድገት ዕድሎች አማካይነት ነው።
10. ቀጣዩን ትውልድ መድረስ
ዶ/ር ስፕሮል እያንዳንዳችንን በእግዚአብሔር የቅድስና መልእክትና በቃሉ እውነት የምንችለውን ብዙ ሰዎች እንድንደርስ ሲሞግተን፣ የአገልግሎታችንን የትኵረት አቅጣጫ አስቀምጧል። ቀጣዩን ትውልድ መድረስ ወሳኝ ጕዳይ ነው። ከኮሌጅና ከከፍተኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋራ በቅርበት እንሠራለን። ምን እንደሚያምኑ፣ ለምን እንደሚያምኑ፣ የሚያምኑትን እንዴት እንደሚኖሩትና ለሌሎችም እንዴት እንደሚያካፍሉት እንዲያውቁትም እናሠለጥናቸዋለን። ይህንም የምናደርገው በአብያተ ክርስቲያናት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በዩኒቨርስቲዎችና በኮሌጃችን ውስጥ ነው፤ እንዲሁም በመተግበሪያዎችና በበይነ መረብ ነው። ታላቁ የሐሳቦች ውይይት፣ ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታን የሚወስን በእውነትና በሐሰት መካከል ያለ ግጭት ሆኗል። መጻኢው ጊዜ በእምነታቸው ለሚጸኑ አማኞች ነው። ዐላማችን፣ የወጣቶቻችንን ነፍስ ለመታደግ በሚደረገው ጦርነት ርዳታን ማቅረብ ነው።
የእግዚአብሔርን ቅድስና በሙላት ማወጅ፣ ማስተማርና መከላከል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ ማዕከላዊ ጕዳይ ነው። ስለ ቅዱሱ አምላካችንና ስለ ቅዱስ ቃሉ ያለውን እውነት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በምናደርገው ጥረት፣ ይህን አገልግሎት እንዴት መደገፍ እንዳለባችሁ ጌታ እንዲያሳያችሁ በጸሎት ስለምትጠይቁና ስለምታስቡ ከልብ እናመሰግናለን። የዛሬው ርዳታችሁ አገልግሎቱን ወደፊት ያራምደዋል። እናመሰግናለን።