እውነተኛ ንስሓ ምን ይመስላል?

20 ሐምሌ 2026

“የሰው ሕይወት ቅዱስና ክቡር ነው” ስንል ምን ማለታችን ነው?

20 ሐምሌ 2026

እውነተኛ ንስሓ ምን ይመስላል?

20 ሐምሌ 2026

“የሰው ሕይወት ቅዱስና ክቡር ነው” ስንል ምን ማለታችን ነው?

20 ሐምሌ 2026

ውስን ስርየት ምንድን ነው?

የውስን ስርየት (Limited atonement) አስተምህሮ፣ የክርስቶስ ስርየት አድማሱና ግቡ ለተመረጡት ብቻ የተወሰነ ነው ይላል። ኢየሱስ በዓለም ላይ ላለ ሰው ሁሉ የኀጢአት ስርየትን አላስገኘም። በእኔ ቤተ እምነት ውስጥ ወደ አገልግሎት የሚገቡ ወጣቶችን እንፈትናለን፤ አንድ ሰው ለተማሪው፣ “በውስን ስርየት ታምናለህ?” ብሎ መጠየቁም አይቀርም። ተማሪውም ሲመልስ፣ “አዎ፣ የክርስቶስ ስርየት ለሁሉም የሚበቃ፣ ለጥቂቶች ደግሞ ውጤታማ መሆኑን አምናለሁ” ይላል። ይህም ማለት በመስቀል ላይ የተከፈለው የክርስቶስ የሞት ዋጋ እስከ ዛሬ በምድር ላይ የኖሩትን ሰዎች ሁሉ ኀጢአት ለመሸፈን የሚበቃ ታላቅ ነው፤ ነገር ግን ተግባራዊ የሚሆነው በክርስቶስ ላይ እምነታቸውን ለጣሉት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ፣ ይህ አባባል በመስቀሉ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ዐላማ የሚዳስሰውን የክርክሩን እውነተኛ ማዕከል አይነካም።

የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ዕቅድ የምንረዳባቸው ሁለት መሠረታዊ መንገዶች አሉ። አንደኛው ግንዛቤ፣ እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ከወደቀው የሰው ዘር መካከል የቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ለማዳን ፍላጎት ነበረው። ስለዚህ የወደቁትን ሰዎች ኀጢአት እንዲሸከም ልጁን ወደ ዓለም የሚልክበትን የደኅንነት ዕቅድ አዘጋጀ የሚል ነው። ኢየሱስ ወደ መስቀል ሄዶ በሆነ ወቅት በርሱ ላይ እምነታቸውን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ይሞታል። ስለዚህ ዕቅዱ ቅድመ ሁኔታን የሚጠብቅ አቅርቦት ነበር። ይኸውም፣ እግዚአብሔር ዕድሉን ለሚጠቀሙበትና ለሚያምኑት ሁሉ ስርየትን አዘጋጅቷል። የዚህ ሐሳብ ፍሬ ነገር፣ ኢየሱስ ለሁሉም ሰው የመዳን ዕድልን (ሊሆን የሚችልን ደኅንነት) ለማስገኘት ሞተ የሚል ነው፤ ነገር ግን በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በዓለም ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የኢየሱስን ሥራ ውድቅ ሊያደርግና በበደሉና በኀጢአቱ ሙት ሆኖ መቅረትን ሊመርጥ ስለሚችል፣ መላው ነገር ከንቱ የመሆን ዕድል አለው። በመሆኑም፣ ማንም ሰው ዕድሉን ባይጠቀምበት የእግዚአብሔር ዕቅድ ሊሰናከል ይችላል። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰፍኖ የሚገኘው አመለካከት ይህ ነው። ይኸውም፣ ኢየሱስ ለሁሉም ሰው ድነትን የሚቻል ከማድረግ አንጻር ሞቷል የሚል ነው። በመጨረሻም፣ ደኅንነት መገኘቱ ወይም አለመገኘቱ በእያንዳንዱ ግለ ሰብ ላይ የተመሠረተ ይሆናል።

ተሐድሷዊው አመለካከት ግን የእግዚአብሔርን ዕቅድ በተለየ መንገድ ይረዳል። እግዚአብሔር ከዘላለም ጀምሮ ያዘጋጀው ዕቅድ ቅድመ ሁኔታን የሚጠብቅ አቅርቦት አልነበረም ይላል። ዕቅዱ፣ ዕቅድ “ሀ” ብቻ ነበር፤ ካልሠራ በሚል የሚከተል ዕቅድ “ለ” አልነበረውም። በዚህ ዕቅድ መሠረት፣ እግዚአብሔር ከወደቀው የሰው ዘር መካከል መጽሐፍ ቅዱስ “ምርጦች” ብሎ የሚጠራቸውን የተወሰኑ ሰዎችን ለማዳን ወሰነ። ያ የምርጫ ዕቅድ በታሪክ ውስጥ እንዲፈጸም፣ ለተመረጡት ሰዎች ደኅንነትን የመፈጸም የተለየ ግብና ንድፍ ይዞ ልጁን ወደ ዓለም ላከ። ይህም ዕቅድ፣ አንድም ጠብታ የክርስቶስ ደም ሳይባክን ፍጹም በሆነ ሁኔታ ተከናወነ። አብ ለደኅንነት የመረጣቸው ሁሉ በስርየቱ አማካይነት ይድናሉ።

ተሐድሷዊ ያልሆነው አመለካከት የሚያመጣው አንድ አንድምታ፣ እግዚአብሔር ማን እንደሚድን አስቀድሞ አያውቅም የሚል ነው። በዚህ ምክንያት፣ ዛሬ አንዳንድ የነገረ መለኮት ምሁራን፣ “እግዚአብሔር ሊያድን የሚችለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ያድናል” ይላሉ። እግዚአብሔር ስንት ሰዎችን ማዳን ይችላል? የማዳን ኀይሉስ እስከ ምን ድረስ ነው? እርሱ በርግጥ አምላክ ከሆነ፣ ሁሉንም የማዳን ኀይል አለው። ሁሉንም የማዳን ሥልጣንስ የለውም? እግዚአብሔር ልክ በሙሴ፣ በአብርሃም፣ ወይም በሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እንደ ገባ ሁሉ፣ የትኛውንም ሰው ከርሱ ጋራ ወዳለ የማዳን ግንኙነት ለማምጣት በማንኛውም ሰው ሕይወት ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልምን? ይህን ለማድረግ በርግጥም መብት አለው።

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “ለዓለም” ስለ መሞቱ እንደሚናገር መካድ አንችልም። ዮሐንስ 3፥16 የዚህ ዐይነቱ አነጋገር ዋነኛው ምሳሌ ነው። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን፣ የዮሐንስን ወንጌል ጨምሮ፣ ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለሰው ሁሉ ሳይሆን “ለበጎቹ” እንደ ሆነ የሚነግረን ሚዛን የሚጠብቅ ሌላ እይታ አለ። እዚህ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ ኢየሱስ በጎቹ አብ ለርሱ የሰጣቸው መሆናቸውን ይናገራል።

በዮሐንስ ምዕራፍ 6 ላይ፣ ኢየሱስ፣ “የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ማንም የለም” ሲል እናያለን (ዮሐንስ 6፥44ሀ)። እዚህ ጋር “መሳብ” ተብሎ የተተረጐመው ቃል በትክክለኛው ትርጕሙ “በኀይል መሳብ/መግፋት”  ማለት ነው። በተጨማሪም፣ ኢየሱስ በዚያው ምዕራፍ ላይ እንዲህ ብሏል፤ “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል” (ዮሐንስ 6፥37ሀ)። የርሱ ሐሳብ አብ ወደ ልጁ እንዲመጡ ያቀዳቸውና የወሰናቸው ሁሉ ይመጣሉ፤ ሌላ ማንም ግን አይመጣም የሚል ነው። ስለዚህ፣ ደኅንነታችሁ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተመሠረተው፣ በጸጋው ሊምራችሁ በወሰነው በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ውሳኔ ላይ ነው፤ ይህንም ያደረገው በእናንተ ውስጥ ያየው የሚገባችሁ ነገር ስላለ ሳይሆን፣ ለልጁ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው። እኔ ክርስቲያን የሆንኩበትን ብቸኛ ምክንያት መናገር ቢኖርብኝ፣ አብ ለልጁ የሰጠው ስጦታ ስለ ሆንኩ ነው እንጂ፣ እኔ ካደረግሁት ወይም ላደርገው ከምችለው ከማንኛውም ነገር የተነሣ አይደለም።


ይህ ዐጭር ጽሑፍ ከአር. ሲ. ስፕሮል የዮሐንስ ወንጌል ማብራሪያ የተወሰደ ነው።

ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው

አር. ሲ. ስፕሮል

አር. ሲ. ስፕሮል

ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች ሲሆን በፍሎሪዳ ሳንፎርድ በሚገኘው በሴንት አንድሪው ቻፕል ውስጥ በስብከትና በትምህርት የሚያገለግል የመጀመሪያው አገልጋይ፣ የሪፎርሜሽን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የቴብልቶክ መጽሔት ዋና አርታዒ ነበር። Renewing Your Mind የተሠኘው የራዲዮ ፕሮግራሙ በየዕለቱ በዓለም ላይ በሚገኙ በመቶዎች በሚቈጠሩ የራዲዮ ጣቢያዎችና በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት አሁንም ድረስ ይደመጣል። The Holiness of God, Chosen by God እና Everyone’s a Theologian የሚሉትን ጨምሮ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጸጽ አልቦነት በመከላከልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በቃሉ ላይ በጽኑ እምነት መቆም እንዳለበት በማስተማር በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።