ውስን ስርየት ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የማድረግ ጥሪ ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

ውስን ስርየት ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የማድረግ ጥሪ ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

“የሰው ሕይወት ቅዱስና ክቡር ነው” ስንል ምን ማለታችን ነው?

በመጽሐፍ ቅዱስ አገላለጽ፣ የሰው ሕይወት ቅድስናና ክቡርነት (sanctity) መሠረቱን የሚጥለው በፍጥረት ላይ ነው። የሰው ዘር እንዲያው በአጋጣሚ የመጣ ድንገተኛ ክሥተት ሳይሆን፣ የዘላለም አምላክ በጥንቃቄ የፈጸመው የፍጥረት ውጤት ተደርጎ ነው የሚታየው። የሰው ልጅ ክቡርነት የሚመነጨው ከእግዚአብሔር ነው። ሰው ውስን፣ ጥገኛና ህልውናው በእግዚአብሔር ላይ የተመሠረተ ፍጥረት ቢሆንም፣ በፈጣሪው ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ ተሰጥቶታል።

በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያለው የፍጥረት ዘገባ ለሰው ልጅ ክቡርነት መሠረቱን ይጥላል፦

“እግዚአብሔር፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍጥረት 1፥26–27)

ሰውን ከሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የሚለየው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ ነው። የእግዚአብሔር መልክና አምሳል ማኅተም፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋራ በተለየ ሁኔታ ያገናኛል። ምንም እንኳ ሰውን እንደ አምላክ ለማየት የሚያስችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ባይኖርም፣ ከፈጣሪው ጋራ ካለው ከዚህ ልዩ ግንኙነት የተነሣ የላቀ ክብር ተሰጥቶታል።

የሰው ልጅ በርግጥ ንጹሕ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሁንም ሰው ነው። ሰው እስከሆንን ድረስ ጠቅለል ባለ መልኩ የእግዚአብሔርን መልክ ይዘናል። አሁንም እጅግ የላቀ ዋጋ ያለን ፍጥረታት ነን። ብቁ ላንሆን እንችላለን፤ ነገር ግን አሁንም ዋጋ አለን። መጽሐፍ ቅዱሳዊ የቤዛነት መልእክት ይህ ነው። እግዚአብሔር ሊቤዣቸውና ሊያድናቸው የተነሣላቸው ፍጥረታት፣ በመጀመሪያ የፈጠራቸው ፍጥረታቱ ራሳቸው ናቸው።

በርካታ የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የሰው ሕይወት ክቡርነት በእግዚአብሔር በመፈጠሩ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ይናገራሉ፤ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  • “ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮኛል፤ የሁሉን ቻዩ አምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጥቶኛል።” (ኢዮብ 33፥4)
  • “እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቁ፤ እርሱ ፈጠረን፤ እኛም የርሱ ነን፤ እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች ነን።” (መዝሙር 100፥3)
  • “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ ከሠሪው ጋራ ክርክር ለሚገጥም ወዮለት! ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣ ‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን? የምትሠራውስ ሥራ፣ ‘እጅ የለህም’ ይልሃልን? አባቱን፣ ‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣ እናቱንም፣ ‘ምን ወለድሽ?’ ለሚል ወዮለት! “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን? ስለ እጆቼስ ሥራ ታዝዙኛላችሁን? ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤ እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤ የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።” (ኢሳይያስ 45፥9–12)
  • “ይህም ሆኖ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አባታችን ነህ፤ እኛ ሸክላዎች፣ አንተም ሸክላ ሠሪ ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን፤” (ኢሳይያስ 64፥8)

የሚገርመው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሕይወት ቅድስናና ክቡርነት ያለውን የብሉይ ኪዳን ዕይታን በተመለከተ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ማብራሪያ ሰጥቷል፦ 

“ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’  እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል።” (ማቴዎስ 5፥21–22)

የኢየሱስ ቃላት ስለ ሕይወት ቅድስናና ክቡርነት ላለን ግንዛቤ ወሳኝ ፋይዳ አላቸው። ኢየሱስ እዚህ ጋር የብሉይ ኪዳን ሕግ ያለውን አንድምታ አስፍቶታል። እርሱ ይናገር የነበረው ዐሥርቱ ትእዛዛትን በተመለከተ ጠባብና ግልብ የሆነ ግንዛቤ ለነበራቸው የሃይማኖት መሪዎች ነበር። በዘመኑ የነበሩት ወግ አጥባቂዎች (legalists) በሕጉ ላይ በግልጽ የተቀመጡትን ነጥቦች ከጠበቁ፣ ስለ ታላቅ መልካምነታቸው ራሳቸውን ማመስገን እንደሚችሉ ርግጠኞች ነበሩ። ይሁን እንጂ የሕጉን ሰፊ አንድምታ መረዳት ተስኗቸው ነበር። በኢየሱስ ዕይታ፣ ሕጉ በዝርዝር ያልገለጻቸው ነገሮች በሰፊው ትርጕሙ ውስጥ በግልጽ ተካትተዋል።

ይህ የሕጉ ባሕርይ ኢየሱስ ማመንዘርን አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ላይም ይታያል፦ 

“ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከርሷ ጋራ አመንዝሯል።” (ማቴዎስ 5፥27–28)

ኢየሱስ በአካል ከሚደረግ የማመንዘር ድርጊት የተቈጠበ ሰው የግድ ሙሉውን ሕግ ታዝዟል ማለት እንዳልሆነ አስረድቷል። ማመንዘርን የሚመለከተው ሕግ ውስብስብ ሲሆን፣ ትክክለኛ ያልሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ብቻ ሳይሆን ከፍትወት እስከ ማመንዘር ድረስ ያለውን ሁሉ ያካትታል። ኢየሱስ ፍትወትን “የልብ ምንዝርና” ሲል ገልጾታል።

ሕጉ የተወሰኑ መጥፎ ባሕርያትንና አመለካከቶችን ከመከልከል ባለፈ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ የተወሰኑ መልካም ባሕርያትንና አመለካከቶችን ይጠይቃል። ይኸውም፣ ማመንዘር ከተከለከለ፣ ጋብቻዊ ንጽሕናና ታማኝነት ይጠበቃሉ ማለት ነው።

እነዚህን በኢየሱስ የተቀመጡትን መርሖች ግድያን በሚከለክለው ሕግ ላይ ስንተገብራቸው፣ በአንድ በኩል በሰፊው የግድያ ትርጕም ውስጥ ከተካተቱ ነገሮች ሁሉ መቈጠብ እንዳለብን እንረዳለን። በሌላ በኩል ግን ሕይወትን ለማዳን፣ ለማሻሻልና ለመንከባከብ እንድንሠራ በአዎንታዊ መልኩ መታዘዛችንን እንገነዘባለን። ከሁሉም ገጽታዎቹና ውጤቶቹ ጋራ ግድያን ማስወገድ ይኖርብናል፤ በተመሳሳይ ጊዜም ሕይወትን ለማቈየት የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን።

ኢየሱስ ፍትወትን የዝሙት አካል አድርጎ እንደ ቈጠረው ሁሉ፣ ያለ በቂ ምክንያት መቈጣትንና ስም ማጥፋትንም እንደ ግድያ አካል አይቷቸዋል። ፍትወት የልብ ምንዝርና እንደ ሆነው ሁሉ፣ ቍጣና ስም ማጥፋትም የልብ ግድያ ናቸው።

ኢየሱስ የዐሥርቱ ትእዛዛትን አድማስ በማስፋት ፍትወትና ስም ማጥፋትን የመሳሰሉ ነገሮችን ሲያካትት፣ ሰውን በፍትወት መመኘት ከአካላዊ ዝሙት እኩል ክፉ ነው ማለቱ አይደለም። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ስም ማጥፋትን ከግድያ ጋራ እኩል ክፉ ነው እያለም አይደለም። እርሱ የተናገረው፣ ግድያን የሚከለክለው ሕግ፣ ባልንጀራን ያለ አግባብ መጕዳትን የሚያካትት ማንኛውንም ነገር የሚከለክል መሆኑን ነው።

ይህ ሁሉ ውርጃን በሚመለከተው ጕዳይ ላይ እንዴት ይሠራል? በኢየሱስ ትምህርት ውስጥ ስለ ሕይወት ቅድስናና ክቡርነት ሌላ ጠንካራ ማረጋገጫ እንመለከታለን። እንደ ስም ማጥፋት ያለ የልብ ግድያ “ ግድያ ሊሆን የሚችል” (potential murder) ክሥተት ተደርጎ ሊገለጽ ይችላል። ሊሆን የሚችል ተግባር የተባለበት ምክንያት፣ ለምሳሌ ቍጣና ስም ማጥፋት ወደ ሙሉ አካላዊ ግድያ የመምራት ዐቅም ስላላቸው ነው። ርግጥ ነው፣ ሁልጊዜ ወደዚያ ውጤት አያመሩም። ቍጣና ስም ማጥፋት የተከለከሉት ወደ ሌላ ከባድ የኀጢአት ድርጊት ስለሚመሩ ብቻ ሳይሆን፣ በመልካም ሕይወት ላይ ከሚያደርሱት እውነተኛ ጕዳት የተነሣ ነው።

ስለ ሕይወት ቅድስናና ክቡርነት የሚደረገውን ውይይት ከውርጃ ጋራ ስናገናኝ፣ ረቂቅ ግን ፈያጅ የሆነ ግንኙነት እንፈጥራለን። ፅንስ አሁን ላይ ሕያው የሰው አካል መሆኑ ባይረጋገጥ እንኳ፣ ሕያው የሰው አካል ሊሆን የሚችል መሆኑ ጥርጥር የለውም። በሌላ አነጋገር፣ ፅንስ በማደግ ላይ ያለ ሰው ነው። ዝም ብሎ ሊሆን የሚችል ሁኔታ ላይ ብቻ የቆመ አይደለም። ፅንሱ ተንቀሳቃሽ በሆነ ሂደት ውስጥ ነው። የውጪ ጣልቃ ገብነት ወይም ድንገተኛ አደጋ ካልገጠመው፣ በርግጥም ሙሉ በሙሉ ወደ ተገለጠ ሕያው የሰው አካልነት ይሸጋገራል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ግድያን የሚከለክለውን ሕግ ትክክለኛውን የግድያ ድርጊትን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ግድያ የሚያመሩ ተግባራትንም እንደሚያካትት ያስተምራል። ኢየሱስ ሕያው በሆነ ሕይወት ላይ ግድያ ሊሆን የሚችል ተግባርን መፈጸም ሕገ ወጥ መሆኑን አስተምሯል። እንግዲህ፣ ሕይወት ሊሆን የሚችል አካል ማጥፋት የሚያስከትለው አንድምታ ምንድን ነው?

ሕይወት ሊሆን የሚችልን አካል ማጥፋትና ሕይወትን ሊያጠፋ የሚችል ክሥተት አንድ አይደሉም። እነዚህ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ባይሆኑም፣ ሕይወት ሊሆን የሚችልን ከማጥፋታችን በፊት ሊመጡ የሚችሉትን ውጤቶች በጥንቃቄ እንድናስብ ለማድረግ ግን በጣም የቀረቡ ናቸው። ይህ የሕጉ ገጽታ ግድያን በሚከለክለው ሰፊና ውስብስብ ሕግ ውስጥ ውርጃን ሙሉ በሙሉ ካላካተተው እንኳ፣ ሁለተኛው ገጽታ በግልጽ ያካትተዋል።

ግድያና ግድያ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን የሚከለክለው የሕጉ አሉታዊ ክልከላዎች፣ ሕይወትን የመጠበቅና የማቈየት አዎንታዊ ትእዛዝን በውስጠ ታዋቂነት ይይዛሉ። ለምሳሌ፣ ዝሙትን የሚከለክለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕግ ጋብቻዊ ንጽሕናና ታማኝነትን ይጠይቃል። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ አንድ ሕግ በአዎንታዊ መልኩ ከተቀመጠ፣ የርሱ ተቃራኒ የሆነው አሉታዊ ነገር በውስጠ ታዋቂነት የተከለከለ ነው። ለምሳሌ፣ እግዚአብሔር የገንዘባችን በጎ ባላደራ እንድንሆን ካዘዘን፣ በግልጽ እንደሚታየው ገንዘብ አባካኞች መሆን የለብንም። ለትጋት ሥራ የተሰጠ አዎንታዊ ትእዛዝ በሥራ ላይ ሰነፍ መሆንን የሚከለክል አሉታዊ ክልከላን በውስጡ ይዟል።

ግድያንና ግድያ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን የሚከለክል አሉታዊ ክልከላ፣ ሕይወትን ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንድንሠራ በውስጠ ታዋቂነት አዎንታዊ ትእዛዝን ይዟል። ግድያን መቃወም ማለት ሕይወት እንዲቀጥል መርዳት ማለት ነው። ውርጃ ሌላ ምንም ነገር ቢያደርግ እንኳ፣ ገና ያልተወለደውን ሕፃን በሕይወት እንዲቀጥል አይረዳም፤ አይጠብቅምም። ምንም እንኳ አንዳንድ ሰዎች ውርጃ ልጅ የማይፈልጉ ሰዎችን የሕይወት ጥራት ያሻሽላል ብለው ቢከራከሩም፣ የጕዳዩ ባለ ቤት የሆነውን በማደግ ላይ ያለውን ያልተወለደ ሕፃን በሕይወት እንዲቀጥል ግን አይረዳም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም የሰው ሕይወት ላለው እጅግ ታላቅ ዋጋና ክቡርነት ዘወትር ጠንካራ ድጋፍ ይሰጣል። ድኾች፣ የተጨቈኑ፣ መበለቶች፣ ወላጅ የሌላቸውና አካል ጕዳተኞች፣ ሁላቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ዋጋ ተሰጥቷቸዋል። ስለዚህ፣ ስለ ውርጃ ጕዳይ የሚደረግ የትኛውም ውይይት፣ በስተመጨረሻ ከዚህ ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ጋራ መታገል ይኖርበታል። የሰው ሕይወት ሊሆን የሚችል አካል እንኳ በቀላሉና በርካሽ ሁኔታ ሲጠፋ፣ የሕይወት ቅድስናንና የሰው ልጅ ክቡርነትን በተመለከተ ባለው አጠቃላይ ዕይታ ላይ ጨለማን ያሰፍናል።


ይህ ዐጭር ጽሑፍ ከአር. ሲ. ስፕሮል “Abortion: A Rational Look at an Emotional Issue” ከተሠኘው መጽሐፍ የተወሰደ ነው።

ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው

አር. ሲ. ስፕሮል

አር. ሲ. ስፕሮል

ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች ሲሆን በፍሎሪዳ ሳንፎርድ በሚገኘው በሴንት አንድሪው ቻፕል ውስጥ በስብከትና በትምህርት የሚያገለግል የመጀመሪያው አገልጋይ፣ የሪፎርሜሽን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የቴብልቶክ መጽሔት ዋና አርታዒ ነበር። Renewing Your Mind የተሠኘው የራዲዮ ፕሮግራሙ በየዕለቱ በዓለም ላይ በሚገኙ በመቶዎች በሚቈጠሩ የራዲዮ ጣቢያዎችና በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት አሁንም ድረስ ይደመጣል። The Holiness of God, Chosen by God እና Everyone’s a Theologian የሚሉትን ጨምሮ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጸጽ አልቦነት በመከላከልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በቃሉ ላይ በጽኑ እምነት መቆም እንዳለበት በማስተማር በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።