ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔር በግ

16 ሐምሌ 2026

ውስን ስርየት ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የእግዚአብሔር በግ

16 ሐምሌ 2026

ውስን ስርየት ምንድን ነው?

20 ሐምሌ 2026

እውነተኛ ንስሓ ምን ይመስላል?

ከንስሓ መዝሙራት አንዱ የሆነው መዝሙር 51፤ ዳዊት በነቢዩ ናታን በተገሠጸ ጊዜ የጻፈው ነው። ናታን ዳዊት ቤርሳቤህን ለራሱ ሚስት አድርጎ በመውሰዱና ባሏን ኦርዮንን በማስገደሉ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ከባድ ኀጢአት መፈጸሙን ተናግሮ ነበር።

ዳዊት የገለጸውን ጥልቅ ሐዘንና ከልብ የመነጨ ጸጸቱን ማስተዋላችን አስፈላጊ ነው። ሆኖም ግን የልብ ንስሓ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑንም መረዳት ይኖርብናል። ዳዊት ንስሓ የገባው መንፈስ ቅዱስ በርሱ ላይ ከሠራው ሥራ የተነሣ ነው። ይህንም ጸሎት ሲጽፍ በመንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ አመራር ሥር ነበር። መንፈስ ቅዱስ እርሱ በልባችን ውስጥ ንስሓን እንዴት እንደሚያመጣ በመዝሙር 51 ላይ ያሳየናል። መዝሙሩን ስንመለከት ይህን ሐሳብ ልብ ልንል ይገባል።

መዝሙር 51 እንዲህ ይጀምራል፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ” (መዝሙር 51፥1)። እዚህ ጋር ለንስሓ መሠረታዊ የሆነ አንድ ነገርን እንመለከታለን። ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው ስለ ኀጢአቱ ሲያውቅና ከርሱም ሲመለስ፣ ራሱን በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ይጥላል። የእውነተኛ ንስሓ የመጀመሪያው ፍሬ ለምሕረት ያለንን ጥልቅ አስፈልጎት መገንዘብ ነው። ዳዊት እግዚአብሔር ፍትሕን እንዲያደርግለት አልጠየቀውም። እግዚአብሔርን በፍትሕ መሠረት ቢይዘው ኖሮ፣ ወዲያውኑ እንደሚጠፋ ያውቃል። በመሆኑም ዳዊት ኑዛዜውን የጀመረው ምሕረትን በመለመን ነው።

ዳዊት እግዚአብሔር መተላለፉን እንዲደመስስለት ሲማጸን፣ እግዚአብሔር ከነፍሱ ላይ ዕድፉን እንዲያስወግድ፣ ዐመፃውን እንዲሸፍንለትና አሁን ዘላቂ የሕይወቱ ክፍል የሆነውን ኀጢአት እንዲያነጻለት እየጠየቀ ነው። በመሆኑም እንዲህ ይላል፤ “በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ” (መዝሙር 51፥2)።

የይቅርታ እና የመንጻት ሐሳቦች ተዛማጅ ቢሆኑም አንድ አይደሉም። በአዲስ ኪዳን ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፤ “ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃም ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው” (1 ዮሐንስ 1፥9)። በንስሓ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት እንቀርባለን፤ ኀጢአታችንንም እንናዘዛለን። የምንጠይቀውም ይቅርታን ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ኀጢአት ደግመን እንዳንሠራ የሚረዳንን ኀይልም ጭምር ነው። ዳዊት በዚህ መዝሙር እንዳደረገው፣ እኛም ወደ ክፋት የሚያዘነብለው ልባችን እንዲወገድ እንጠይቃለን።

ዳዊት በመቀጠል፣ “እኔ መተላለፌን ዐውቃለሁና፤ ኀጢአቴም ዘወትር በፊቴ ነው” ይላል (መዝሙር 51፥3)። ይህ ዝም ብሎ በደልን አምኖ መቀበል ብቻ አይደለም። እርሱ በበደለኛነት ስሜት የሚሠቃይ ሰው ነው፤ “በደለኛ መሆኔን ዐውቃለሁ” እያለ ነው። በደሉን ለማሳነስ አልሞከረም። ራስ ጸደቅ ለመሆንም አልታገለም። እኛ ግን በአንጻሩ ምክንያቶችን በመደርደርና ለኀጢአተኛ ባሕርያችን ሰበቦችን በመስጠት የተዋጣልን ነን። ነገር ግን በዚህ ክፍል ውስጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት እውነተኛ ሆኖ ቀርቧል። በደሉን አምኗል፤ ኀጢአቱም ዘወትር በፊቱ እንዳለ ተረድቷል። ከርሱ ሊገላገል አልቻለም፤ ይህም እጅግ የሚያስጨንቀው ሆኗል።

ከዚያም እንዲህ ሲል ይጮኻል፤ “አንተን፣ በርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ” (መዝሙር 51፥4)። በአንድ በኩል ዳዊት እዚህ ጋር ግነትን እየተጠቀመ ነው። እርሱ በኦርዮን፣ በኦርዮን ቤተ ሰቦችና ጓደኞች፣ በቤርሳቤህና በመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከባድ ኀጢአትን ፈጽሟል። ነገር ግን ዳዊት ኀጢአት በዋናነት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም በደል መሆኑን ተረድቷል፤ ምክንያቱም በዚህ አጽናፈ ዓለም ውስጥ ብቸኛው ፍጹም አካል እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ፈራጅ እንደ መሆኑ መጠን፣ ኀጢአት ሁሉ የሚተረጐመው የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስና በቅድስናው ላይ እንደሚደረግ በደል ነው። ዳዊት ይህን ያውቃል፤ ያምነዋልም። ኀጢአቱ በሰዎች ላይ ያደረሰውን በደል እውነታን እያሳነሰ አይደለም፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ያደረሰውን  ከፍ ያለ በደል ተገንዝቧል።

ቀጥሎም ብዙ ጊዜ ትኲረት የማይሰጠውን አንድ ንግግር ያደርጋል። ይህ በቍጥር 4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ የእውነተኛ ንስሓ መግለጫዎች መካከል አንዱ ነው፦ “በቃልህ ትጸድቅ፣ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ፣” (መዝሙር 51፥4)። ዳዊት እያለ ያለው፦ “አምላክ ሆይ፣ በእኔ ላይ የመፍረድ ሙሉ መብት አለህ፤ ከፍርድህና ከቍጣህ በቀር ሌላ ምንም ነገር እንደማይገባኝ ግልጽ ነው”። ዳዊት እግዚአብሔር እንከን የሌለበት መሆኑንና በርሱ ላይ የመፍረድ ሙሉ መብት እንዳለው አምኗል። ከእግዚአብሔር ጋራ ምንም ዐይነት ድርድር ወይም ሙግት ውስጥ አልገባም።

“ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ። እነሆ፤ እውነትን ከሰው ልብ ትሻለህ፤ ስለዚህ ጥልቅ ጥበብን በውስጤ አስተምረኝ” (መዝሙር 51፥5-6)። እግዚአብሔር ከእኛ እውነትን ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው፣ ያ እውነት ከውስጣችን ጥልቅ ክፍል እንዲመነጭም ይፈልጋል። ዳዊት እግዚአብሔር ያዘዘውን ለማድረግ እንደተሳነው፣ እንዲሁም የርሱ መታዘዝ ብዙ ጊዜ ከማንነቱ ማዕከል ከሚመነጭ ድርጊት ይልቅ ውጫዊ ሥርዐት ብቻ እንደ ነበር አምኗል።

ከዚያም ዳዊት እንደ ገና ለመንጻት ይጮኻል፦ “በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ፤ ዕጠበኝ፤ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ” (መዝሙር 51፥7)። በዳዊት ድምፅ ውስጥ ፍጹም ዐቅመ ቢስነትን እንሰማለን። ዳዊት፦ “አምላክ ሆይ፣ አንድ አፍታ ቈይ። ይህን የጸሎት ንግግር ከመቀጠሌ በፊት እጄን መታጠብ አለብኝ፤ መታጠብ ይኖርብኛል” አላለም። ዳዊት የበደለኛነት ዕድፉን ከራሱ ላይ ለማስወገድ ዐቅም እንደሌለው ያውቃል። ካሣ ሊከፍል አይችልም። እኛም ኀጢአታችንን ማስተስረይ እንደማንችል በማመን ከዳዊት ጋራ መተባበር አለብን።

በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል እግዚአብሔር በኋላ ላይ ይህን ተስፋ ሰጥቷል፦ “ኑና እንዋቀሥ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ፣ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም፣ እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል (ኢሳይያስ 1፥18)። እግዚአብሔር በጭቃ ውስጥ ተዘፍቀን ሲያገኘን ሊያነጻን ይወድዳል።

ዳዊት በመቀጠል፣ “ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ” (መዝሙር 51፥8ሀ) ይላል። ንስሓ አሠቃቂ ነገር ነው። ኀጢአትን በመናዘዝና በደለኛነትን አምኖ በመቀበል ሂደት ውስጥ የሚያልፍ ማን ይደሰታል? የበደለኛነት ስሜት ደስታን ከሚያጠፉ ነገሮች ሁሉ በላይ ኀይለኛ ነው። ዳዊት በዚያ ቅጽበት በጣም ደስተኛ ባይሆንም፣ እግዚአብሔር ነፍሱን እንዲያድሳትና ደግሞ ደስታንና ሐሴትን እንዲሰጠው ይጠይቃል። ይህንም ነጥብ፣ “ያደቀቅሃቸው ዐጥንቶቼም ደስ ይበላቸው” በሚለው ንግግሩ ያጐላዋል (መዝሙር 51፥8ለ)። ይህ አስደናቂ አገላለጽ አይደለምን? እንዲህ እያለ ነው፦

“አምላክ ሆይ፣ ቀጥቅጠኸኛል። አጥንቶቼ ተሰብረዋል፤ አጥንቶቼን የሰበረው ሰይጣን ወይም ናታን ሳይሆን፣ አንተ ስለ በደሌ በወቀሥኸኝ ጊዜ አንተ ነህ የሰበርካቸው። ስለዚህ፣ እንደ ተሰበረ ሰው በፊትህ ቆሜአለሁ፤ መቀጠል የምችለው አንተ ከፈወስኸኝና ደስታንና ሐሴትን ከመለስህልኝ ብቻ ነው።”

በመቀጠልም እንዲህ ይላል፤ “ፊትህን ከኀጢአቴ መልስ፤ በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ። አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” (መዝሙር 51፥9-10)። ንጹሕ ልብ ሊኖረን የሚችለው መለኮታዊ በሆነው የዳግም ፍጥረት ሥራ ብቻ ነው። ያንን በራሴ ውስጥ የመፍጠር ዐቅም የለኝም። ንጹሕ ልብን ሊፈጥር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ እርሱ ኀጢአታችንን በመደምሰስ ንጹሕ ልብን ይፈጥራል።

ከዚያም ዳዊት፣ “ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ” በማለት ይጮኻል (መዝሙር 51፥11)። ዳዊት የትኛውም ኀጢአተኛ ሊደርስበት የሚችለው ከሁሉ የከፋው ነገር ይህ መሆኑን ተረድቷል። ንስሓ ሳንገባ ብንጸና፣ እግዚአብሔር በርግጥ ከፊቱ እንደሚጥለን ያውቃል። ኢየሱስ እርሱን የሚቃወሙ ለዘላለም ከእግዚአብሔር እንደሚለዩ አስጠንቅቋል። ነገር ግን የንስሓ ጸሎት ለአማኙ መጠጊያ ነው። ኀጢአት ውስጥ መሆኑን ለሚያውቅ ሰው እግዚአብሔርን የመምሰል ምላሽ ነው። እንዲህ ዐይነቱ ምላሽ ዳግም የተወለዱ ሰዎች ሁሉ የሕይወት መታወቂያ ሊሆን ይገባል።

ዳዊት፣  “የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ። እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” በማለት ይቀጥላል (መዝሙር 51፥12-13)። ክርስቲያኖች በትዕቢት የተሞላ፣ ራስን ጻድቅ የማድረግ ወይም “ከእኔ በላይ ቅዱስ የለም” የሚል አመለካከትን ስለሚያሳዩ ሰዎች በክርስቲያኖች መካከል መገኘት ደስ እንደማይላቸው ብዙ ጊዜ ሲናገሩ እንሰማለን። ነገር ግን ይህ መሆን የለበትም። ክርስቲያኖች የሚኲራሩበት ምንም ነገር የላቸውም፤ እኛ ዐመፀኞችን ለማረም የምንሞክር ጻድቃን አይደለንም። አንድ ሰባኪ እንደተናገረው፦ “ወንጌልን መስበክ ማለት አንዱ ለማኝ ለሌላው ለማኝ የት ዳቦ እንደሚያገኝ ሲናገር ማለት ነው።” በአማኝና በማያምን መካከል ያለው ዋነኛው ልዩነት ይቅርታ ነው። አንድ ሰው በክርስቶስ ስም አገልጋይ ለመሆን ብቁ የሚያደርገው ብቸኛው ነገር፣ ያ ሰው ይቅርታን የቀመሰና ያንን ለሌሎች መናገር የሚፈልግ መሆኑ ነው።

“ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል። መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም። እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” (መዝሙር 51፥15-17)። 

የትንቢታዊ ንስሓ ልብና ነፍስ የሚገኘው እዚህ ጋር ነው። እግዚአብሔርን የመምሰል ንስሓ እውነተኛ ተፈጥሮ፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም” በሚለው ሐረግ ውስጥ ይገኛል። ዳዊት የራሱን ኀጢአት ማስተስረይ ቢችል ኖሮ እንደሚያደርገው እየተናገረ ነው፤ ነገር ግን ባለበት ሁኔታ፣ ብቸኛ ተስፋው እግዚአብሔር በምሕረቱ እንዲቀበለው ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን እንደሚቃወም፣ ለትሑታን ግን ጸጋን እንደሚሰጥ በግልጽ ይነግረናል፤ በተግባርም ያሳየናል። ዳዊት ይህ እውነት መሆኑን ያውቃል። ምንም ያህል ቢሰበርም፣ እግዚአብሔርንና እግዚአብሔር ንስሓ ከሚገቡ ሰዎች ጋራ ያለውን ግንኙነት ያውቃል። እግዚአብሔር የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ ከቶ እንደማይጠላ ወይም እንደማይንቅ ተረድቷል። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው ይህን ነው። ኢየሱስ በአንቀጸ ብፁዓን ላይ፣ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና” ሲል በአእምሮው የነበረው ይህ ነው (ማቴዎስ 5፥4)። ይህ ክፍል የምንወድደውን ሰው በሞት ስናጣ የሚሰማን ማዘን ብቻ ሳይሆን፣ በኀጢአታችን ተወቅሠን የምንለማመደውን ሐዘንም ይጨምራል። ኢየሱስ ስለ ኀጢአታችን ስናዝን፣ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንደሚያጽናናን ያረጋግጥልናል።

ክርስቲያኖች ሁሉ መዝሙር 51ን በቃላቸው እንዲያጠኑ እመክራለሁ። ይህ መዝሙር እግዚአብሔርን የመምሰል ንስሓ ፍጹም ምሳሌ (Model) ነው። በሕይወቴ ብዙ ጊዜ ወደ ጌታ መጥቼ፣  “አምላክ ሆይ፤ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ” ወይም “መተላለፌን ደምስስ፤ በሂሶጵ እርጨኝ፤ እኔም እነጻለሁ” ብያለሁ። ብዙ ጊዜ፣ “ጌታ ሆይ፤ የማዳንህን ደስታ መልስልኝ” ብዬ ጸልዬአለሁ፤ እንዲሁም፣ “አንተን፣ በርግጥ አንተን ብቻ በደልሁ፤ በፊትህም ክፉ ነገር አደረግሁ” ብዬ ጮኼአለሁ። በበደለኛነታችን እውነታ ስንዋጥ፣ በእግዚአብሔር ፊት በንስሓ ራሳችንን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩናል። በእነዚያ ወቅቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ራሳቸው በከንፈሮቻችን ላይ መኖራቸው በርግጥም በረከት ነው።


ይህ ጽሑፍ ከአር. ሲ. ስፕሮል What Is Repentance? ከተሠኘው የጥያቄና መልስ መጽሐፍ የተወሰደ ነው።

ይህ አምድ በመጀመሪያ የታተመው በሊጎኔር ሚኒስትሪስ ብሎግ ነው

አር. ሲ. ስፕሮል

አር. ሲ. ስፕሮል

ዶ/ር አር. ሲ. ስፕሮል የሊጎኔር ሚኒስትሪስ መሥራች ሲሆን በፍሎሪዳ ሳንፎርድ በሚገኘው በሴንት አንድሪው ቻፕል ውስጥ በስብከትና በትምህርት የሚያገለግል የመጀመሪያው አገልጋይ፣ የሪፎርሜሽን መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንትና የቴብልቶክ መጽሔት ዋና አርታዒ ነበር። Renewing Your Mind የተሠኘው የራዲዮ ፕሮግራሙ በየዕለቱ በዓለም ላይ በሚገኙ በመቶዎች በሚቈጠሩ የራዲዮ ጣቢያዎችና በኢንተርኔት በቀጥታ ሥርጭት አሁንም ድረስ ይደመጣል። The Holiness of God, Chosen by God እና Everyone’s a Theologian የሚሉትን ጨምሮ፣ ከመቶ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ጽፏል። የመጽሐፍ ቅዱስን ሕጸጽ አልቦነት በመከላከልና የእግዚአብሔር ሕዝብ በቃሉ ላይ በጽኑ እምነት መቆም እንዳለበት በማስተማር በዓለም ዙሪያ ይታወቃል።